የኮሮናቫይረስ ህመም ምልክቶችና በበሽታው ላለመያዝ ማድረግ ያለብን ጥንቃቄ

አፏን ሸፍና የምታስል ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮሮናቫይረስ በዓለም ዙሪያ ባሉ ከሰማኒያ በላይ አገራት ውስጥ ተዛምቶ 130 ሺህ ያህል ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለሞት ተዳርገዋል።

በዚህም ሳቢያ ወረርሽኙ የወቅቱ የዓለም ሕዝብ ስጋት ሆኗል።

ስለዚህ ስለበሽታው ምንነትና እራስን ለመከላከል መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ ጠቃሚ መረጃዎችን እነሆ።

የኮሮናቫይረስ በሽታ ምልክቶች የትኞቹ ናቸው?

የኮሮናቫይረስ የመተንፈሻ አካላት በሽታ ሲሆን ሲጀምር በትኩሳት ሲሆን በማስከተልም ደረቅ ሳል ይነረዋል። ከሳምንት በኋላ ደግሞ የትንፋሽ ማጠርን ያስከትላል፤ በዚህ ሳቢያም አንዳንድ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የህክምና እርዳታ ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

የእነዚህ ምልክቶች መታየት ግን በበሽታው የመያዝ ምልክት ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም ምልክቶቹ ከተለመዱት የጉንፋንና የኢንፍሉዌንዛ ምልክቶች ጋር ተመሳሳይ ነው።

ኮሮናቫይረስ የከፋ በሚሆን በት ጊዜ ኒሞኒያን፣ ሳርስን፣ የውስጥ አካላት ሥራ ማቆምን እንዲሁም ሞትን ሊያስከትል ይችላል።

በዕድሜ የገፉና አስም፣ የስኳር በሽታ፣ የልብ ህመምን የመሳሰሉ ቀደም ሲል የነበሩ የጤና ችግሮች ያሉባቸው ሰዎች በበሽታው ሲያዙ በጠና የመታመም ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

ሰዎች በበሽታው ከተያዙ በኋላ ምልክቶችን እስከሚያሳዩ ድረስ እስከ 14 ቀናትን ሊወስድ እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል። ነገር ግን አንዳንድ አጥኚዎች ምልክት የማየቱ ነገር አስከ 24 ቀናት ድረስ ሊቆይ እንደሚችል ጠቁመዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እንዴት እራሴን መጠበቅ እችላለሁ?

የጤና ተቋማት እንደሚሉት በሽታውን ለመከላከል እጅን በመደበኝነት በደንብ መታጠብ እጅግ ጠቃሚ ነው።

እስካሁን በሽታው እንዴት እንደሚተላለፍ በእርግጠኝነት የሚታወቅ ነገር የለም። ነገር ግን የኮሮና አይነት ቫይረሶች በበሽታው የተያዙ ሰዎች በሚያስሉበትና በሚያስነጥሱበት ወቅት በሚያወጧቸው ጥቃቅን ጠብታዎች አማካይነት ነው።

ስለዚህም ስናስልና ስናስነጥስ አፍንጫና አፋችንን በሶፍት ወይም በክርናችን እንሸፍን፤ ፊታችንን እጃችንን ሳንታጠብ አንንካ። በተጨማሪም ከታመሙ ሰዎች ጋር የቀረበ ንክኪ ከማድረግ መቆጠብ በሽታውን ለመከላከል ያግዛል።

የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች የሚፈለገውን ያህል በሽታውን ለመከላከል አያስችሉም።

'የኮሮናቫይረስ አለብኝ ብዬ ካሰብኩ ምን ማድረግ አለብኝ?'

በበሽታው ተይዣለሁ ብለው የሚያስቡ ሰዎች አስፈላጊውን ምክርና የህክምና ድጋፍ ለማግኘት ለሚመለከታቸው የጤና ተቋማት ማሳወቅ አለባቸው።

በበሽታው ተያዞ ይሆናል ተብሎ ከሚታሰብ ሰው ጋር የቀረበ ንክኪ ከነበረዎት፤ እራስዎን ለተወሰነ ጊዜ ከሌሎች ሰዎች አግልለው እንዲቆዩ ሊነገርዎት ይችላል። ስለዚህ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር የሚኖርን የቀረበ ንክኪ ማስወገድ ይኖርብዎታል።

በሽታው ከተከሰተባቸውና ከሌሎች አገራት የተመለሱ ከሆነ ምናልባትም ለተወሰነ ጊዜ እራስዎን አግልለው መቆየት ሊያስፈልግዎት ይችላል።

ኮሮናቫይረስ ምንያህል አደገኛ ነው? ሊድንስ ይችላል?

የዓለም ጤና ድርጅት ከ56 ህሙማን ላይ በሰበሰበው መረጃ መሰረት በኮሮናቫይረስ ከተያዙ አምስት ሰዎች መካከል አራቱ ቀለል ያሉ የበሽታውን ምልክቶች ብቻ ያሳያሉ። በዚህም መሰረት፡

  • 80 በመቶው ቀለል ያሉ ምልክቶችን ያሳያሉ
  • 14 በመቶው ከባድ ምልክቶችን ያሳያሉ
  • 6% በመቶው ክፉኛ ይታመማሉ

ምንም እንኳን አሃዞቹ አስተማማኝ ባይሆኑም በበሽታው ከተያዙት መካከል የሚሞቱት ሰዎች ብዛት ዝቅተኛ እንደሆነ ተስተውሏል፤ ይህም ማለት በበሽታው ከተያዙ ሰዎች መካከል ከመቶው አንድ ወይም ሁለቱ ብቻ የሚሆኑት ናቸው ለሞት የሚዳረጉት።

በአሁኑ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩት በህክምና ላይ ያሉ ሲሆን ሊሞቱ ይችላሉ። በዚህም ሳቢያ የሞት መጠኑ በመቶኛ ከፍ ሊል ይችላል።