ኮሮናቫይረስ፡ ሰሜን ኮሪያ 'ተለይተው' የነበሩ ዲፕሎማቶችን ለቀቀች

ኮሮናቫይረስ፡ ሰሜን ኮሪያ 'ተለይተው' የነበሩ ዲፕሎማቶችን ለቀቀች

የፎቶው ባለመብት, JOACHIM BERGSTROM/TWITTER

ሰሜን ኮሪያ ውስጥ ከኮሮናቫይረስ ስጋት ጋር በተያያዘ በለይቶ ማቆያ እንዲቀመጡ ተፈርዶባቸው የነበሩ 60 ያክል ዲፕሎማቶች ተለቀው ሩስያ ገቡ።

ወደ ሩስያዋ ቭላዲቮሶስቶክ ከተማ ያቀናው አውሮፕላን በውስጡ በርካታ የውጭ አገር ዲፕሎማቶችን ይዞ ነበር። ሰሜን ኮሪያ፤ ከዋና ከተማዋ ፒዮንግያን ተነስቶ ወደ ተቀረው ዓለም አውሮፕላን ሲበርባት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይህ የመጀመሪያው ነው።

የበረራ ቁጥር KOR271 በምሥራቃዊቷ የሩስያ ከተማ ሰኞ ማለዳ አርፏል።

ኤምባሲዎች ውስጥ የሚሠሩ በርካታ ሰዎች ወርሃ ጥርና የካቲት መባቻን ከሚኖሩበት ግቢ ንቅንቅ እንዳይሉ ተደርገው ነበር።

ሰሜን ኮሪያ ኮሮናቫይረስ እንዳይስፋፋ በሚል ስጋት የውጭ አገር ዲፕሎማቶችን ሰብስባ ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲገቡ ያደረገችው ባለፈው ወር ነበር።

የሩስያው አምባሳደር አሌክሳንደር ማስቴጎራ የነበረው ሁኔታ 'ሞራል አድቃቂ' ሲሉ ነበር የገለፁት።

ሰሜን ኮሪያ እስካሁን በኮሮናቫይረስ የተያዘብኝ ሰው የለም ብትልም የሕክምና ሰዎች ግን ጥርጣሬ አላቸው። ሰሜን ኮሪያ ቫይረሱ ከመነጨባት ቻይና እና ቫይረስ ብዙ ጉዳት ካደረሰባት ደቡብ ኮሪያ ጋር መዋሰኗ 'ጥርጣሬያቸውን እውነት ይሆን እንዴ' የሚያስብል ነው።

ቢያንስ 60 ይሆናሉ የተባሉት ዲፕሎማቶችና የኤምባሲ ሠራተኞች ወደየአገራቸው መቼ ይመለሳሉ ለሚለው ቁርጥ ያለ ምላሽ የለም።

በሰሜን ኮሪያ የታላቋ ብሪታኒያ አምባሰደር የሆኑት ኮሊን ክሩክስ፤ ሰኞ ጠዋት በትዊተር ገፃቸው 'የጀርመንና ፈረንሳይ ኤምባሲ ወዳጆቼን መሰናበቴ ቅር አሰኝቶኛል' ሲሉ ለጥፈዋል። ጨምረውም ሰሜን ኮሪያ የሚገኙ ኤምባሲዎች ለጊዜው ቢዘጉም የብሪታኒያ ኤምባሲ ክፍት ሆኖ ይቆያል ብለዋል።

ሰሜን ኮሪያ ከዚህ በፊት በኮሮናቫይረስ ስጋት 380 ያክል የውጭ አገራት ዲፕሎማቶችን ከመኖሪያ ግቢያቸው ለ30 ቀናት እንዳይወጡ ብላ ማገዷ አይዘነጋም።

የኪም መንግሥት ዕግዱን ያነሳው ባለፈው ሳምንት ነበር።

የስዊድን አምባሳደር የሆኑት ዮዋኪም በርገስቶርም ከተለቀቁ በኋላ "ኪም ጆንግ ሱንግ ሁለተኛ አደባባይ ላይ ቆሜ ደስተኛ እሆናሉ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር ሲሉ" ትዊተራቸው ላይ ተውተዋል።

አሁንም ቢሆንም ሰሜን ኮሪያ የሚገኙ ዲፕሎማቶች ከሰሜን ኮሪያ ጋር እንዲገናኙ አይፈቅድላቸውም፤ ምግብ ቤት፣ ሱቅ፣ ጂም እና ሆቴሎችን መጎበኝት አይችሉም ሲል ኤንኬ የሰተኘው የሰሜን ኮሪያ ዜና ጣብያ ዘግቧል።

ኮሮናቫይረስ ሰሜን ኮሪያ ቢገባ አገሪቱ የመመርመሪያም ሆነ የማከሚያ አቅሙ የላትም የሚል ከፍተኛ ስጋት አለ።

እስካሁን በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 3600 ሲሆን ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ደግሞ 107 ሺህ ናቸው።