ሂዩማን ራይትስ ዋች ቡድኑ መንግሥት በምዕራብ ኦሮሚያ ኢንተርኔትና ስልክን እንዲከፍት ጠየቀ

የኢትዮጵያ ካርታ

ለሁለት ወራት በምዕራብ ኦሮሚያ ተዘግቶ የቆየውን የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲከፍት ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠየቀ።

የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳለው የአገልግሎቶቹ መቋረጥ ቤተሰቦች መካከል ያለውን ግንኙነትንና ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችን ከማስተጓጎሉ በተጨማሪ መንግሥት በአካባቢው በታጣቂዎች ላይ እያካሄደ ያለውን ዘመቻ በተመለከተ የመረጃ ግርዶች እንዲፈጠር አድርጓል ብሏል።

ከታኅሳስ 23/2012 ዓ.ም ጀምሮ የሞባይል ስልክ፣ የመደበኛ ስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቶች በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙት የቄለም ወለጋ፣ የምዕራብ ወለጋና ሆሮጉድሩ ዞኖች ውስጥ ተቋርጦ መቆየቱን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በምሥራቅ ወለጋ ደግሞ በከተሞች አካባቢ ብቻ የጽሑፍ መልዕክትና የሞባይል አገልግሎት ቢኖርም የኢንተርኔትና የማህበራዊ ሚዲያ አገልግሎቶች ዝግ እንደሆኑ ነዋሪዎች ተናግረዋል ብሏል።

የአገልግኦቶቹ መዘጋት የተከሰተው የመንግሥት ኃይሎች የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ታጣቂ ኃይል በሆነው ቡድን ላይ ዘመቻ በከፈተባቸው አካባቢዎች ሲሆን በቦታዎቹ "ግድያና የጅምላ እስርን ጨምሮ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች" መዘገባቸውን ሂዩማን ራይት ዋች ገልጿል።

የድርጅቱ የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላይቲታ ባደር፤ የግንኙነት አገልግሎቶቹ መቋረጥ በአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ችግርን እያስከተለ በመሆኑ መንግሥት በአስቸኳይ በመክፈት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ቡድኑ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስተዳደር ስር ማኅበራዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች በሚያጋጥሙበት ወቅት ካለምንም ምክንያት የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶችን ማቋረጥ እየተለመደ መጥቷል ብሏል።

ማዕከላዊው መንግሥት ስለአገልግሎቶቹ መቋረጥ ምንም አይነት ማብራሪያ ባይሰጥም ጠቅላይ ሚኒስርቱ ፓርላማ ቀርበው እንዳረጋገጡት እርምጃው የተወሰደው "በጸጥታ ምክንያት ነው።" የገዢው ፓርቲ ቃል አቀባይ እርምጃው ከሚካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ጋር ግንኑነት የለውም ነገር ግን ለዘመቻው መሳካት አስተዋጽኦ አድርጓል ማለታቸውን ድርጅቱ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

"ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሕጎች ሰዎች ኢንተርኔትን ጨምሮ በየትኛውም አማራጭ በነጻነት መረጃን ማግኘትና ማስተላለፍን ይደግፋሉ። ከጸጥታ ጋር የተገኛኘ ክልከላም ሕግን መሠረት ማድረግና ለተባለው ችግርም ተመጣጣኝ መሆን ይገባዋል። ግልጽነት በጎደለው ሁኔታ የግኙነት መስመሮችን ማቋረጥና የሚቆይበት የጊዜ ርዝመት የመብት ጥሰትን ሊጋብዝ ይችላል" ብሏል ድርጅቱ።

መግለጫው አክሎም ባጋጠመው የግንኙነት መስመሮች መቋረጥ ሳቢያ አራት የበጎ አድራጎት ድርጅቶች በሥራቸው ላይ እንቅፋት እንደገጠማቸው መናገራቸውን በመግለጽ፤ ሁኔታው በአካባቢዎቹ ባለው የጤና አገልግሎት አቅርቦትም ላይ ጫና መፍጠሩን ሰራተኞችን ጠቅሶ በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል። በተጨማሪም በእርምጃው ሳቢያ ቤተሰብ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲቋረጥ ማድረጉናና ተማሪዎችም መቸገራቸውን ገልጿል።

ቀደም ሲል ተቃውሞዎች በተቀሰቀሱበት ወቅት፣ በፈተናዎች ጊዜና የሰኔ 15ቱ ግድያ ወቅት የኢንትርኔት አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን በእነዚህ ጊዜያት "መንግሥት ስለአገልግሎቱ መቋረጥም ሆነ መቼ እንደሚመለስ ምንም አይነት ማብራሪያ አልሰጠም" ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ገልጿል።

ወታደራዊ ዘመቻው በሚካሄድባቸው የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ስላለው የስልክ አገልግሎት መቋረጥን በተመለከተ በአካባቢው የአገር መከላከያ ሠራዊት እየወሰደው ካለው ኦፕሬሽን ጋር የተያያዘ መሆኑን ከሁለት ሳምንት በፊት የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም የሆኑት ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ለቢቢሲ አረጋግጠው ነበር።

ኤታማዦር ሹሙ አክለውም "የስልክ አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጉ በአካባቢው በታጣቂዎቹ ላይ የሚወሰደውን እርምጃ ስኬታማ አድርጎታል" ብለውም ተናገረዋል።

መንግሥት ታጣቂዎች ለማደን ያደርገው የነበረው ዘመቻ እንቅፋት ገጥሞት እንደነበረና የስልክ አገልግሎት እንዲቋረጥ መደረጉ "በጣም ነው የጠቀመን" ያሉት ጀነራል ብርሃኑ፤ ታጣቂዎቹ "የሞባይል ስልክ በመጠቀም ነው የመንግሥትን እንቅስቃሴ ለሁለት ዓመት ሲያከሽፉ የቆዩት" ብለው ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።