መንግሥት በፖለቲካ ፓርቲዎችና መገናኛ ብዙሃን ላይ እርምጃ እወስዳለሁ አለ

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ የሆኑትን አቶ ንጉሡ ጥላሁን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መንግሥት የሕዝብን አንድነትና አብሮነት እንዲሸረሸር በሚያደርጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙሃን ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ማስታወቁን ፋና ዘገበ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ የሆኑት አቶ ንጉሡ ጥላሁን "በሕዝባዊ መድረኮችና በመገናኛ ብዙሃን በኩል የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮች በአገር አንድነትና አብሮነት ላይ አደጋ ይደቅናሉ" ማለታቸውን ፋና ገልጿል።

ኃላፊው ጨምረውም በመሰል ድርጊት በሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙሃን ላይ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንና ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን መንግሥት ተገቢና ተመጣጣኝ ዕርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ መናገራቸውን ገልጿል።

በትናንትናው ዕለት ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን በተመለከተ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ያካሄደው ዝግጅት ላይ የተደረገውን ንግግር ኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦኤምኤን) ማስተላለፉን በተመለከተም ኃላፊነቱ የሁለቱም ወገኖች መሆኑን ተናግረዋል።

"ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌን የጣሰና ኢትዮጵያዊ ዕውነታን ያላገናዘበ የጥላቻ ንግግር ለዘመናት በአብሮነት ወደኖሩ ሕዝቦች መተላለፉን ተከትሎ ፓርቲውም ሆነ የመገናኛ ተቋሙ ተገቢውን ኃላፊነት መውሰድ አለባቸው" ሲሉ አሳስበዋል።

ትናንት አዳማ ላይ የነበረው ዝግጅት በኦኤምኤን በቀጥታ የተላለፈ ሲሆን አንዲት ተሳታፊ ያቀረበችው ሃሳብ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል፤ ቪዲዮውም ከአማርኛ ትርጉሙ ጋር በስፋት ሲዘዋወር ነበር።

ጉዳዩ መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ ውግዘትና ቁጣን በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ አስተናግዷል። ይህንንም ተከትሎ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግርማ ጉተማ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ክስተቱን በተመለከተ የይቅርታ መልዕክት አስፍረዋል።

አቶ ግርማ በጽሁፋቸው ኦኤምኤን ዝግጅቱን በቀጥታ እያስተላለፈ እንደነበርና ንግግሩን ማቋረጥ እንደነበረባቸው አምነው ነገር ግን እንዳልቻሉ አመልክተዋል። ነገር ግን ንግግሩ ካበቃ በኋላ ወዲያው ከማኅበራዊ ሚዲያና ከሳተላይት ላይ እንዲወርድ መደረጉን ገልጸዋል።

ጨምረውም "በዚህ ከቁጥጥራችን ውጭ በሆነ ምክኒያት ኦኤምኤን ላይ ላኮረፋችሁ ተመልካቾቻን ሁሉ ይቅርታ እንጠይቃለን" ብለዋል።

አቶ ንጉሡ ለፋና ጉዳዩን በተመለከተ የተፈጠረው ነገር ስህተት ብቻ ሳይሆን ጥፋት መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ንጉሡ መንግሥት ለረጅም ጊዜ በመማማርና በመመካከር ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴን አማራጭ አድርጎ በትዕግስት መቆየቱንም አመልክተዋል።

አሁን ግን በአገሪቱ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ተግባራት በግልፅ እየተበራከቱ በመምጣታቸው መንግሥት እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንና ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በዚህ ረገድ የሚስተዋሉ ክፍተቶች በፍጥነት እንዲታረሙ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አቶ ንጉሡ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንም ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ ያተኮሩና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ መገናኛ ብዙሃንን እንደማይታገስና በአዋጁ መሰረትም እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንደሰን አንዷለም መናገራቸውን ፋና ጨምሮ ገልጿል።

በዚህም መሰረት በኦኤምኤን ላይ የተላለፈው መልዕክት ሙሉ ተንቀሳቃሽ ምስል ባለስልጣኑ እንደደረሰውና መልዕክቱ በባለሙያዎችና አመራሮች እየተገመገመ በመሆኑ በአጭር ጊዜ መረጃውን በማጥራት ውጤቱ ይፋ እንደሚደረግም ገልጸዋል።