ሱዳን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የግድያ ሙከራ ላይ ምርመራ ጀመረች

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብደላ ሐምዶክ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የሱዳን ባለስልጣናት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አብደላ ሐምዶክ ላይ ተፈጸመ በተባለው የግድያ ሙከራ ላይ ምርምራ ማድረግ መጀመራቸውን ገለጹ።

የአገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጽህፈት ቤታቸው እየሄዱ በነበረበት ጊዜ ይጓዙበት የነበረውንና ያጀቧቸው ተሽከርካሪዎች ኢላማ በማድረግ በፈንጂና በተኩስ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰ የተዘገበ ሲሆን ሐምዶክ ከጥቃቱ በኋላ ደህና መሆናቸውን አሳውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸውና የተሻለ ጥበቃ ወዳለበት ቦታ መወሰዳቸውን የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

ማኅበራዊ ሚድያዎች ላይ የተለጠፉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች የፕሬዝደንቱና የአጃቢዎቻቸው መኪና መስታወቶች ረግፈው ያሳያል።

ከጥቃቱ በኋላ በመንግሥት ቴሌቪዥን ላይ በቀረበ ምስል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የሚገኝበትን የዋና ከተማዋን ማዕከላዊ ክፍል ከሰሜናዊ ካርቱም ጋር በሚያገናኘው ኮበር ድልድይ ላይ በጥቃቱ የተጎዱ መኪኖች ታይተዋል።

የጸጥታ ሰራተኞች ጥቃቱ የተፈጸመበትን ቦታ በመለየት ተቆጣጥረው የምርመራ ሥራ ተጀምሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብደላ ሐምዱክ በይፋዊ የትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ደህና መሆናቸውንና ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባቸው አሳውቀዋል። ጨምረውም ዛሬ እሳቸውን ያጋጠማቸው ጥቃት አገራቸው ሱዳን እያካሄደችው ያለውን ሽግግር እንደማያደናቅፈው ገልጸዋል።

ሱዳን ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ለ30 ዓመታት የመሯትን ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽርን ከስልጣን ያስወገደው ለወራት የዘለቀ ሕዝባዊ ተቃውሞ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አሁን ድረስ በዘለቀ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሱዳን ተቃዋሚ ቡድኖችና በጦር ሠራዊቱ መካከል የተደረሰውን የሥልጣን ክፍፍል መሰረት የተቋቋመውን የሽግግር መንግሥት በመምራት ላይ ይገኛሉ።

ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስርሩን የገጠማቸው ጥቃት ሱዳን ውስጥ አሁንም የቀጠለውን አስተማማኝ ያልሆነ ሁኔታ የሚጠቁም ነው ተብሏል።

የአዲስ አበባው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መሥሪያ ቤት ምክትል ኃላፊ ሆነው ያገለገሉት ሐምዶክ የሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ባለፈው ነሐሴ ላይ ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ ቢሮ ኃላፊ «ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነበሩበት መኪና ላይ ፈንጂ ቢወረወርም ፈጣሪ ይመስገን ማንም አልተጎዳም» ሲሉ ሁኔታውን ገልፀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ኃላፊ ኤኤፍፒ ለተሰኘው የዜና ወኪል የግድያ ሙከራውን በተመለከተ ዝርዝር መረጃ እንደሚወጣ ተናግረዋል። እስካሁን ለአደጋው ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም።