ኮሮኖቫይረስ፡ እውን ነጭ ሽንኩርት የኮሮናቫይረስ ጠር ነው?

ነጭ ሽንኩርት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮሮናቫይረስ ከአገር አገር እየተስፋፋ ነው። በየቀኑ አዳዲስ አገራት 'ኧረ እኛም አገር ገባ እኮ' እያሉ ነው። እስካሁን ኮሮናን ውልቅ አድርጎ የሚያስወጣ ሐኪሞች ያጨበጨቡለት መድኃኒት አልተገኘም።

'እነ ነጭ ሽንኩርትና ባሕር ዛፍ ምን ሠርተው ይበላሉና' የሚል ምክር ሰምተው ይሆናል።

ዓለም በአንድ ስጋት ስትናጥ ተከትሎ የሚመጣ አንድ ፅንሰ-ሐሳብ አለ፤ በእንግሊዝ አፍ 'ኮንስፓይረሲ ቲየሪ' ይሰኛል፤ የሴራ ፅንሰ-ሐሳብ ብለን እንተርጉመው።

ወደ ኢንተርኔት ዓለም ብቅ ቢሉ ወሬው ሁሉ ስለኮሮናቫይረስ ነው፤ የወቅቱ የዓለም ስጋት ነውና። ኮሮናን ይከላከላሉ ተብሎ የሚወራላቸው ደግሞ ብዙዎች ናቸው። ነጭ ሽንኩርት ደግሞ የአጥቂ መስመር ላይ ተሰልፋለች።

ነጭ ካባ ከደረበ ዶክተር. . .

ነጭ ሽንኩርት ዝናዋ በዓለም የናኘ ነው። የፌስቡክ ገፅ ቢኖራት ኖሮ 6 ቢሊዮን ሕዝብ የሚከተላት ነጭ የደረበች ሽንኩርት. . . ። ነጭ ሽንኩርት ፌስቡክ ለመቆጣጠር ገፅ አላሻትም። የኮሮናቫይረስን መፈወሻ ተበለው ፌስቡክ ላይ ዝናቸው ከናኘ ነገሮች መካከል ነጭ ሽንኩርት አንደኛ ነች። ግን ኮሮናን መከላከልም ሆነ ማዳን ትችል ይሆን?

ዶ/ር ቴድሮስ የሚመሩት የዓለም ጤና ድርጅት ግን እንዲህ ይላል - ነጭ ሽንኩርት ብሉ በውስጡ መልካም ነገር አዝሏልና፤ ነገር ግን ከአዲሱ ቫይረስ ሊከላከል እንደሚችል በሳይንስ አልተረጋገጠም።

እርግጥ የዶ/ር ቴድሮስ መሥሪያ ቤት እንዳለው ነጭ ሽንኩርት በልኩ መብላት ይመከራል። ከኮሮናቫይረስ ጋር ግን የሚያገናኘው ነገር የለም።

ደቡብ ቻይና ውስጥ ከኮሮናቫይረስ ይታደገኛል ብለው 1.5 ኪሎ ግራም ነጭ ሽንኩርት 'ዱቄት' ያደረጉ አንዲት ሴት ጉሮሯቸው ተቃጥሎ በሕክምና ነው የዳኑት።

የዓለም ጤና ድርጅት፤ ፍራፍሬና ጥራጥሬ እንዲሁም አትክልት በልኩ ተመገቡ፤ ውሃም ጠጡ ይላል። ነገር ግን ይላል ድርጅቱ. . . ነገር ግን ኮሮናን ይታደጋል ተበሎ ፈቃድ የወጣለት ምንም ዓይነት ምግብ እስካሁን አልተገኘም።

ተዓምረኛ ንጥረ-ነገሮች

ዩቲዩበኛው ጆርዳን ሳዘር በተለያዩ ማኅበራዊ ድር-አምባዎች ላይ ብዙ ሺህ ተከታዮች አሉት። ይህ ግለሰብ አንድ 'ኤምኤም የተሰኘ ተዓምራዊ ንጥረ-ነገር የኮሮናቫይረስን ድራሽ ማጥፋት ይችላል' እያለ ይሰብካል።

ንጥረ ነገሩ ክሎራይን ዳይኦክሳይድ የተሰኘ አንጭ ኬሚካል አዝሏል። ጆርዳንና መሰሎቹ ክሎራይን ዳይኦክሳይድ ያለበት ኤምኤም የካንሰር ሴልን ያጠፋል እያሉ ይሰብኩ ነበር። አሁን ደግሞ ለኮሮናቫይረስ ፍቱን መድኃኒት ነው ብለው ብቅ ብለዋል።

ባለፈው ዓመት የአሜሪካ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር ይህንን ኬሚካል መጠጣት ለጤና እጅግ አስጊ ነው ሲል ማስጠንቀቂያ አውጥቶ ነበር። መሥሪያ ቤቱ ይህንን ኬሚካል የምትጠጡ ወዮላችሁ፤ ኬሚካሉ በሽታ እንደሚከላከል የሚጠቁም ጥናት የለም ሲል ነው ያስጠነቀቀው።

አልፎም ኬሚካሉ ሰውነት ውስጥ ያለ ፈሳሽን አሟጦ በመጨረስ ለከፍተኛ የውሃ ጥም ሊያጋልጥ ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

'ሳኒታይዘር' ጨርሰናል የሚሉ ማስታወቂያዎች ማየት እየተለመደ መጥቷል

ጓዳ ሠራሽ 'ሳኒታይዘር'

«ባለሱቅ፤ ሳኒታይዘር አለ?»

«ውይ! አንድ ቀርታ ነበር። እሷን ደግሞ ለእኔ . . .»

ከመዳፎቻችን ላይ ባክቴሪያ ነሽ ቫይረስ እንዲሁም ቆሻሻ ያስወግዳሉ የሚባልላቸው 'ሳኒታይዘሮች' [ተህዋሲያን ማጽጃ ፈሳሽ] ከገበያ እየጠፉ ነው።

ጣልያን ውስጥ ነው አሉ። የሳኒታይዘር እጦት የወሬ ሟሟሻ ሆነ። ኮሮናቫይረስ ሰቅዞ የያዛት የጣልያን ነዋሪዎች ታድያ ወደ ኩሽና ገቡ። የተገኘውን ነገር መቀላቀል ጀመሩ። በአገሬው ዘንድ ታዋቂ የሆነ አንድ ኬሚካል ግን ቆዳ እንዲያፀዳ ሳይሆን እምነ-በረድ እንዲያፀዳ የተሰናዳ ነው።

በተለይ ደግሞ ውስጣቸው በመቶኛ ከፍ ያለ የአልኮል መጠንን ያዘሉ ፈሳሾች ለመቀየጫነት ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው። የዓለም የጤና ድርጅት ደግሞ የምንጠቀማቸው ሳኒታይዘሮች ቢያንስ ከ60-70 በመቶ የአልኮልነት መጠን ቢኖራቸው ሲል ይመክራል።

ነገር ግን ሳይንቲስቶች ኩሽና ውስጥ ቫይረስና ባክቴሪያ የሚገድል 'ሳኒታይዘር' ማምረት ከባድ ነው ይላሉ። ቮድካ እንኳ 40 በመቶ ብቻ የአልኮል ይዘት ነው ያለው።

እና ሌሎች. . .

ከላይ ከተጠሱት አልፎ የቀለጠ ሲልቨር መጠጣት፣ ውሃ በ15 ደቂቃ ልዩነት መጠጣ [የሞቀ ውሃማ ፍቱን ያሉም አልጠፉም]፣ ሙቀት ማግኘት እና አይስ ክሬም አለመላስ የኮሮናቫይረስን ለመፈወስ ፍቱን ናቸው ተብለው በማኅበራዊ ድር-አምባዎች ማስታወቂያ የተሠራላቸው ናቸው።

ሳይንሱ ግን እስካሁን የተረጋገጠ ፈውስ አልተገኘም ይላል። ነገር ግን በሽታውን ለመከላከል ዋናውና ቀላሉ መፍትሔ እጅን በሳሙን በደንብ ፈትጎ መታጠብ፣ የእርስ በርስ ንክኪን መቀነስ፣ ፊትን በእጅ አለመነካካት፣ በሽታው ካለበት ሰው ጋር ንክኪ አለማድረግ. . . ነው።

አደራዎትን 1 ኪሎ ነጭ ሽንኩርት ስልቅጥ አድርገው በጠላ ካወራረዱ በኋላ እንደ ዉሃኗ ነዋሪ ርዕሰ-አንቀፅ እንዳይሆኑ። ሐኪም ያላዘዘውን መጠቀም ጠንቅ ነውና!