በመንዝ ጌራ መሐል ሜዳ ትናንት ምሽት በተፈጸመ ጥቃት አራት ሰዎች ተገደሉ

ካርታ

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን መንዝ ጌራ ወረዳ በመሐል ሜዳ ከተማ አንድ ግለሰብ በፈጸመው ጥቃት የአራት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ አስራ ስድስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የአካባቢው ባለስልጣናት ለቢቢሲ ገለጸ።

ሰኞ ምሽት አንድ ሠዓት ከሩብ ላይ ኤፍ ዋን በተባለ የእጅ ቦንብ፣ በሽጉጥና በጩቤ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ በአስራ ስድስት ሰዎች ላይ ደግሞ የመቁሰል ጉዳት መድረሱን የመንዝ ጌራ ወረዳ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ት ቤት ኃላፊ አቶ ጌትነት አጎናፍር ተናግረዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው መሐል ሜዳ ከተማ ቀበሌ ሦስት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለ አንድ መጠጥ ቤት ውስጥ በነበሩ ሰዎች ላይ ሲሆን፤ ይህንን ጥቃት የፈጸመው ግለሰብ የመጠጥ ቤቱ ባለቤት ልጅ ባል የሆነ ግለሰብ እንደሆነና ሚስቱን ለመግደል የፈጸመው ድርጊት እንደነበረ የመሃል ሜዳ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ጥላሁን ደበበ አብራርተዋል።

ግለሰቡ የኋላ የወንጀል ታሪክ እንዳለውም የተናገሩት ፖሊስ አዛዡ ከአሁን በፊትም ከ15 ዓመት በላይ አብራው የኖረችው ሚስቱን በሽጉጥ ተኩሶ ሲስታት፤ ወንድሟን አቁስሎ ታስሮ የነበረ ሲሆን፤ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተፈትቶ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሂደት ላይ ነው ብለዋል።

ትናንት ምሽት የፈጸመው ጥቃትም ባለቤቱን ለመግደል መሆኑንና ጥቃት የተፈጸመበት ቤትም የሚስቱ እናት ቤት መሆኑን ኢንስፔክተር ጥላሁን ገልጸዋል። ጥቃቱ ሲፈጸም ሚስቱ በቦታው የነበረች ቢሆንም ጉዳት እንዳልደረሰባትም አመልክተዋል።

ከሞቱት ሰዎች ሁለቱ በሽጉጥ በተተኮሰባቸው ጥይት ሲሆን አንደኛው ደግሞ ግለሰቡ ባፈነዳው ቦንብ እንደሆነ ተነግሯል።

ግለሰቡ በመጠጥ ቤቱ ውስጥ በነበሩ ሰዎች ላይ ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላም መንገድ ላይ ያገኘውን የ16 ዓመት ታዳጊ በጩቤ በፈጸመበት ጥቃት ክንዱ ላይ ጉዳት በማድረስ እንዳቆሰለውም አቶ ጌትነት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሽጉጥና በቦምብ ጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል ሦስቱ ወዲያውኑ ህይወታቸው እንዳለፈ ከአካባቢው ነዋሪዎች ቢቢሲ ያረጋገጠ ሲሆን፤ የመቁሰል ጉዳት ከደረሰባቸው 16 ሰዎች መካከል ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ስድስቱ እዚያው ከተማ ሃኪም ቤት ተኝተው ህክምና እያገኙ ሲሆን ሦስቱ ግን ለተጨማሪ ህክምና ወደ ደብረ ብርሃን መላካቸውን የፖሊስ ኃላፊው አረጋግጠዋል።

የተቀሩት ደግሞ የደረሰባቸው ቀላል ጉዳት በመሆኑ የመጀመሪያ የህክምና እርዳታ አግኝተው ወደ ቤታቸው መመለሳቸው ተነግሯል።

የኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ጌትነት አጎናፍር አክለውም ክስተቱ ከዚሁ ጋር እንደሚያያዝ ለጊዜው ያልተረጋገጠ ቢሆንም በተመሳሳይ ሰዓት እዚያው መሐል ሜዳ ከተማ ውስጥ አንድ ግለሰብ ጭንቅላቱ ላይ በመጥረቢያ ተመትቶ ሞቶ መገኘቱን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በሟቹ ግለሰብ ኪሱ ውስጥ ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያም ሆነ መረጃ ባለመገኘቱ እስካሁን ማንነቱን ለመለየት እንዳልተቻለ ተናግረዋል። ግለሰቡ ተገድሎ የተገኘበት ቦታ በቦምብና በጥይት ጥቃት ከተፈጸመበት አካባቢ ቢያንስ በአንድ ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ የሚገኝ እንደሆነም ታውቋል።

ሦስት ሰዎች የሞቱበትና በርካቶች የቆሰሉበት ጥቃት የተፈጸመበት መጠጥ ቤት በከተማዋ ለረጅም ጊዜ የቆየና ባለቤቷም ወይዘሮ ትርንጎ የመግደል ሙከራው የተደረገባት ሚስት እናት ሲሆኑ በጥቃቱ በሽጉጥ ከተመቱት አንዷ መሆናቸውን አቶ ጌትነት ተናግረዋል።

በጥቃቱ በአጠቃላይ 16 ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ከመጠጥ ቤቱ ባለቤት ወይዘሮ ትርንጎ ውጪ ሁሉም ወንዶች ሲሆኑ፤ በከተማዋ በሌላ ቦታ ላይ ተገድሎ የተገኘውን ሰው ጨምሮ የአራት ሰዎች ሕይወት አልፏል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ቤት ውስጥ በርካታ ሰዎች የነበሩ ሲሆን ከሞቱትና ከቆሰሉት ውጪ ብዙዎቹ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው እንደተረፉ አቶ ጌትነት ተናገረዋል።

ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ ሸሽቶ ያመለጠ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ፖሊስና የአካባቢው የጸጥታ አካላት መንገዶችን ዘግተው ፍተሻ በማድረግ ተጠርጣሪውን ለመያዝ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ኢንስፔክትር ጥላሁን ደበበ ለቢቢሲ ተናግረዋል።