ቻይና ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ያደረገችውን ፍልሚያ በቅርብ የተመለከተው የኢትዮጵያዊው ዶክተር ምልከታ

ዉሃን ከታሕሳስ ወር አጋማሽ ጀምሮ እንቅስቃሴ ተገድቦ ነበር

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ,

ዉሃን ከታሕሳስ ወር አጋማሽ ጀምሮ እንቅስቃሴ ተገድቦ ነበር

በቻይና ህክምና ለማጥናት ከአምስት ዓመታት በላይ ቆይቷል። በጥቅሉ በኢትዮጵያና በቻይና ህክምና በማጥናትና በዘርፉ በማገልገልም ጭምር አስር ዓመት ገደማ መቆየቱን ይናገራል።

ምንም እንኳ እሱ የሚኖርበት የቻይና ከተማ በኮሮናቫይረስ ከተጠቁት የቻይና አካባቢዎች የተሻለ የሚባለው ቢሆንም መንግሥት በአጠቃላይ የወሰደው እርምጃ ቻይና የቫይረሱን ስርጭት መግታት እንድትችል አድርጓል ይላል።

ስሙን መጥቀስ ያልፈለገው ይህ በቻይና የሚሰራው ኢትዮጵያዊ የህክምና ባለሙያ የሆነው ዶክተር የኮሮናቫይረስን ስርጭት በመቆጣጠር በኩል ኢትዮጵያ ከቻይና የምትማረው በርካታ ነገሮች አሉ ብሎ ያምናል።

ለዚህም ኅብረተሰቡ እጁን ቶሎ ቶሎ እንዲታጠብ ማሳሰብ፣ የትምህርት ቤቶችን መዘጋት፣ በርካታ ሰው የሚገኝባቸውን ትላልቅ ስብሰባዎች አለመካሄድ ከተካሄዱም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እውቅና እንዲሆኑ ማድረግና ሌሎችም የኢትዮጵያ መንግሥት በአግባቡ መውሰድና ተፈጻሚ ማድረግ ካለበት ወሳኝ እርምጃዎች መካከል ቀዳሚ መሆናቸውን ይጠቅሳል።

ነገር ግን እሱ ቻይና ውስጥ ካስተዋለው ልምድ በመነሳት የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛን መጠቀም ላይ ትኩረት ቢያደርግ ወረርሽኙን ለመከላከል እንደ አንድ ጥሩ አማራች ሊሆን ይችላል ይላል።

ምንም እንኳን የዓለም የጤና ድርጅትና የአገራት የጤና ባለስልጣናት ሁሉም ሰው ጭምብል ማድረግ የለበትም ቢሉም እሱ ግን "ሃኪሞች፣ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችና አስታማሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ይህን ሰፋ አድርጎ ብዙዎች እንዲጠቀሙ ማድረግ ያስፈልጋል" በማለት ጥቅም እንጂ ጉዳት እንደሌለው ያመለክታል።

ዶክተሩ በቅርብ ከተመለከተው ልምዱ በመነሳት እንደሚለው ከሆነ ማኅበራዊ ርቀትን ለመጠበቅ በማያስችሉ ቦታዎች በተለይም በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ፣ በገበያዎች፣ ቤተ እምነቶች ውስጥ እንዲሁም በርካታ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ላይ የሰዎች ጭንብል መጠቀም የቫይረሱን ስርጭት በተወሰነ መልኩ በመገደብ ረገድ ወሳኝ እንደሆነ በቻይና መመልከቱን ይናገራል።

የህክምና ባለሙያው ደጋግሞ በአጽንኦት እንደሚለው ሰዎች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ላይ ማስክ ማድረግ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነገር አይደለም።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የሞባይል ስልኮችን ማፅዳት እንዲሁም ሰዎች ከቤት ውጭ ሳሉ የነካኳቸውን ነገሮች ቤት ገብተው ማፅዳትም አስፈላጊ ነው። "ለምሳሌ በእጅ የተነካኩ አትክልቶችን በሚገባ ማጠብ ያስፈልጋል። ምንም እንኳ እጃችንን ብንታጠብም እንደ ስልክ ያሉ ነገሮችን ስንነካ መልሶ ያው ይሆናል።"

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኙባቸው አካባቢዎችን ይፋ ማድረግና አካባቢው ላይ ያሉ ሰዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማድረግ ቻይና የተከተለችው አንድ መንገድ ነው። ይህን ማድረግ ምናልባትም በኢትዮጵያ ማግለል እና ሌሎች ያልተገቡ ነገሮችን ሊያስከትል ቢችልም ይህ ተገቢ እንዳልሆነ አስገንዝቦ ሰዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ መረጃውን መስጠት ይጠቅማል ይላል።

የኮሮናቫይረስ ህሙማንን የሚያክሙ የህክምና ባለሙያዎች በየቀኑ ወደቤታቸውን ከሚመላለሱ ይልቅ በሚሰሩበት ሆስፒታል ወይም ቅርብ አካባቢ ጊዜያዊ መቆያ ቢዘጋጅላቸው በብዙ መልኩ መልካም እንደሆነም በመግለጽ፣ "የአገሪቱ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይህን እየሰራበት እንደሚሆን አምናለሁ" በማለት፤ ይህ በኅብረተሰቡ ውስጥ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እንደሚረዳ ይጠቅሳል።

ከጣልያን ጋር በማነፃፀር ቻይና እጅግ በሚያስገርም መልኩ የቫይረሱን ስርጭት ተቆጣጥራዋለች የሚሉት ባለሙያው የተያዙ ሰዎች የመሞት እድልም አነስተኛ እንደሆነ ይገልጻል፤ ባለሙያው አክሎም ምንም እንኳ በቻይና በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም የሟቾች ቁጥር ግን ትንሽ የሚባል አንደሆነ ያስረዳል።

በበሽታው የተጠረጠሩ ወይም ቫይረሱ ካለባቸው ጋር ግንኙነት ነበራቸው በሚል ተለይተው እንዲቀመጡ የተደረጉ ሰዎችን በተመለከተም እነዚህ ሰዎች በሙሉ ቫይረሱ ላይገኝባቸው ስለሚችል አንድ ቦታ ላይ እንዲቆዩ ሲደረግ በኋላ ላይ በምርመራ ሊገኝ የሚችለውን ውጤት ታሳቢ በማድረግ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ይገልፃል።

በበሽታው ስጋት ሳቢያ ራሳቸውን አግልለው የሚቆዩ ሰዎች ንፅህናን መጠበቅና አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባቸው ሲሆን መንግሥትም እነዚህ ሰዎች የሚከታተልበት የራሱ ሥርዓት ሊኖረው ይገባል ሲል ይመክራል።

ለዚህም በምሳሌነት የጠቀሰው ቀደም ብለው "ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ተማሪዎች ሌሎችን ለመጠበቅ ሲሉ በራሳቸው ወጪ እንግዳ ማረፊያ ይዘው ራሳቸውን አግልለው የቆዩበት መንገድ የሚመሰግን ነው" በማለት አንስቷቸዋል።

በረራዎችን በሚመለከት ማንኛውም ወደ አገር የሚገባ መንገደኛ ራሱን አግልሎ እንዲቆይ መደረጉ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን የሚጠቅሰው ይህ የህክምና ባለሙያ፤ ከመንገደኞች ጋር ግንኙነት ያላቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች ጭንብል ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ያምናል።

በእምነት ተቋማት ላይም የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት የሚያሳስበው ባለሙያው፤ በደቡብ ኮሪያ በአንድ ቤተ እምነት ውስጥ በሚሰባሰቡ ሰዎች መካከል ወረርሽኙ በመዛመቱ ብዙዎች በቫይረሱ መያዛቸውንና ለሞትም የተዳረጉ መኖራቸውን በመጥቀስ ቤተ እምነቶች ላይ ትልቅ ሥራ እንዲሰራ፤ ቁጥጥርም እንዲደረግ ያሳስባል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ዉሃን ከታሕሳስ ወር አጋማሽ ጀምሮ እንቅስቃሴ ተገድቦ ነበር

በአገር ውስጥ ሊኖር የሚችለውን የአስፈላጊ ነገሮችን እጥረት በማሰብም በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንደ የፊት መሸፈኛ ጭንብል እና ሳኒታይዘርን የመሳሰሉ ነገሮችን ቢለግሱ የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ አስተዋፅዖ ነው ይላል።

ጭንብል ማድረግ አስፈላጊ በሆኑባቸው ቦታዎች ላይ የማግኘት ችግር ቢኖር እንኳን እንደ ስካርፍ ባሉ አልባሳት አፍና አፍንጫን መሸፈን ከምንም እንደሚሻል ባለሙያው ይመክራል። ስለዚህ በዚህ ወቅት "ጉንፋን እንኳን ላለመያዝ እያንዳንዱ ሰው ጥረት ማድረግ ይኖርበታል።"

ባለሙያው እንደሚለው ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀስቅሶባቸው በነበሩ አካባቢዎች ላይ መደበኛ የህክምና ባለሙያዎች እና ባህላዊ ህክምና ባለሙያዎች አንድ ላይ ያደረጉት ርብርብ ቻይና የቫይረሱን ስርጭት በሚገባ እንድትቆጣጠር ረድቷል ብሎ ያምናል።

በተጨማሪም የህክምና ባለሙያዎች ችግሩ የእኔ ነው በሚል መንፈስ በትጋት መስራታቸውና ኅብረተሰቡም የሚተላለፍለትን ማሳሰቢያ ያለ አንዳች ቸልተኝነት መፈፀሙ እንዲሁም የአገሪቱ መንግሥት ኃላፊነቱን በትጋት መወጣቱ ቻይናን እንደታደጋት ይገልፃል።