ኮሮናቫይረስ፡ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተጣለውን ዕገዳ ለማምለጥ የጥድፊያ ጋብቻዎች በአውስትራሊያ

ጥንዶች Image copyright Getty Images

የአውስትራሊያ ባለስልጣናት በጋብቻ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ከአምስት ሰው በላይ እንዳይገኝ እገዳ ሊያደርጉ መሆኑን ካስታወቁ በኋላ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በርካታ ጥንዶች ጋብቻቸውን በጥድፊያ ፈጽመዋል።

መንግሥት ሰዎች በብዛት እንዳይሰበሰቡ ለማድረግ ያወጣው እገዳ በጋብቻ ሥነ ሥርዓቶች ላይ የሚገኙት አምስት ሰዎች ሙሽራውንና ሙሽሪትን የሚጨምር ነው ተብሏል።

እገዳው ተግባራዊ ይሆን የነበረው ረቡዕ እኩለ ሌሊት ላይ ስለነበረ በርካቶች ቀደም ብለው ያቀዱትን የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን ብዛት ያላቸው ታደሚ በተገኙበት ለማክበር ሲሉ ቀድመው አካሂደዋል።

ከእገዳው በኋላ ባለው ጊዜ ጥቂት ሰው በሚገኝበት ጋብቻን መፈጸም፣ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ጋብቻውን ማራዘም የተቀመጡ አማራጮች ናቸው። በተጨማሪም በተጋቢዎች በተፈቀደው ቁጥር ሥነ ሥርዓቱን በማካሄድ በኢንትርኔት አማካይነት ወዳጅ ዘመዶቻቸው ከያሉበት ሆነው እንዲታደሙ ማድረግ ይችላሉ ተብሏል።

በእገዳው ምክንያት ጋብቻዋን ኩንስላንድ ውስጥ በሚገኝ በአንድ ፓርክ ውስጥ ያደረገችው የቴሌቪዥን ጋዜጠኛዋ ቢንዲ ኢርዊን የቅርብ ዘመዶቿ ብቻ በሥነ ሥርዓቱ ላይ መታደማቸውን ተናግራለች።

"ለአንድ ዓመት ያህል ለዚህ ቀን ስንዘጋጅ ብንቆይም ሁሉንም ነገር ለመቀየር ተገደናል፤ በሠርጋችን ላይ እንግዶች አልነበሩንም ነበር" በማለት የሆነውን ጽፋለች።

"ይህ ውሳኔያችን በጣም አስቸጋሪ ውሳኔ ነበር፤ ነገር ግን ለሁሉም ሰው ደኅንነት ስንል ማድረግ የነበረብን ጠቃሚ ነገር ነው" ስትል አክላለች።