ኮሮናቫይረስ፡ ሴንጋፖር አካላዊ እርቀትን የማይጠብቁ ሰዎችን በገንዘብና በእስር ልትቀጣ ነው

አካላዊ እርቀት መጠበቅን Image copyright Getty Images

ሴንጋፖር የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ከሚመከሩት መንገዶች አንዱ የሆነውን በሰዎች መካከል መኖር ያለበትን አካላዊ እርቀት መጠበቅን ተግባራዊ የማያደርጉ ሰዎችን በገንዘብና በእስር ልትቀጣ ነው።

ትናንት እኩለ ሌሊት ላይ ተግባራዊ በተደረገው በዚህ ውሳኔ መሰረት አካላዊ እርቀታቸውን ሳይጠብቁ የተገኙ ሰዎች እስከ 7 ሺህ ዶላር የሚደርስ የገንዘብ ቅጣት፣ አስከ ስድስት ወራት የሚደርስ እስር ወይም በሁለቱም ሊቀጡ ይችላሉ ተብሏል።

መንግሥት ከዚህ በተጨማሪ አዲስ መመሪያ ተግባራዊ እንደሚያደርግም እየተነገረ ነው፤ ይህም ከሰዎች ከአንድ ሜትር ባነሰ እርቀት ላይ ሆነው ሆነ ብለው የሚያስሉ ሰዎች ደንብ እንደጣሱ ተቆጥረው ሊቀጡ እንደሚችሉም ተነግሯል።

ነገር ግን አንድ ሰው ሆነ ብሎ ማሳሉን በሚመለከት እንዴት ሊታወቅ እንደሚችል አጠያያቂ ሆኗል።

በሴንጋፖር ሕዝቡ መንግሥት ያዘዘውን እንዲፈጽም እንዲህ ያለውን ከበድ ያለ ቅጣት የተለመደ ሲሆን፤ ዜጎችም ያለምንም ማመንታት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ይነገራል።

ሴንጋፖር በሽታው አሳሳቢ ደረጃ ካልደረሰባቸው አገራት መካከል ስትሆን ምግብ ቤቶችና ካፌዎች ክፍት ሲሆኑ እዚያም አካላዊ እርቀትን መጠበቅ የግድ ነው። በተጨማሪም መስሪያ ቤቶችና ትምህርት ቤቶች መደበኛ ተግባራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ ተብሏል።

ምንም እንኳን ሴንጋፖር የኮሮናቫይረስን በመቆጣጠር በኩል ላደረገችው ጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትን ያገኘች ሲሆን፤ ዜጎች ግን ትምህርት ቤቶች እስካሁን ድረስ ክፍት ሆነው በመቆየታቸው ደስተኞች አይደሉም ተብሏል።

በአንዳንድ አጸደ ህጻናትና በዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ባሉ ሰራተኞች ላይ የበሽታው ፍንጮች በመታየታቸው ወረርሽኙ በሕዝቡ ውስጥ በስጋት ሊሰራጭ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

ተያያዥ ርዕሶች