ኮሮናቫይረስ ቤተሰብን ያቀራርብ ወይስ ያራርቅ ይሆን?

ኮሮናቫይረስ ቤተሰብን ያቀራርብ ወይስ ያራርቅ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኮሮናቫይረስ የመላው ዓለም ራስ ምታት ሳይሆን በፊት ጥንዶች በአማካይ በቀን ውስጥ ወደ ሁለት ሰዓት ተኩል ብቻ አብረው ያሳልፉ እንደነበር ጥናቶች ያሳያሉ። አሁን ነገሮች ተለዋውጠዋል።

በተለይም አንዳንድ አገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የዜጎቻቸውን እንቅስቃሴ ከገደቡ በኋላ ጥንዶች በቀን እስከ 16 ሰዓት ገደማ አብረው ይሆናሉ። ልጆቻቸውም ከቤት አይወጡም።

ታድያ ይህንን ሁሉ ሰዓት በአንድ ቤት ማሳለፍን ላልለመዱ ቤተሰቦች ወቅቱ ጭንቅ ሆኖባቸዋል።

ጊዜው ቤተሰቦችን ያቀራርብ ይሆን ወይስ ቤት ውስጥ ውጥረት ይነግሥ ይሆን?

የኦፕን ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ጃኩዊ ጋብ "እንዲህ ያለ [ከቤት መውጣት የተከለከለበት] አኗኗር ገጥሞን አያውቅም" ይላሉ። የቤተሰብን የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚፈትንበት ወቅት እንደሆነ ያመለክታሉ።

በዚህ ላይ ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ በእርግጠኛነት አለማወቅ፣ ስለ ገንዘብ መጨነቅ፣ ቀድሞ ያዝናኑን የነበሩ ተግባሮች ማከናወን አለመቻል እና ስለ በሽታው አብዝቶ ማሰብ ተጨምረዋል።

የወቅቱ ሥነ ልቦናዊ ጫና የሥነ ልቦና ተመራማሪዋ ዶ/ር ካሮላይን ሹስተር እንደሚሉት፤ ብዙዎች በዚህ ወቅት ነፃነት ማጣት ሊሰማቸው ይችላል። "ነፃነት ማጣት፣ መደበት እና የመገለል ስሜት ይገጥማል" ይላሉ።

ዶ/ር ካሮላይን እና ፕ/ር ጃኩዊ የቤት ውስጥ ጥቃት ይጨምራል የሚል ስጋት አላቸው። ለምሳሌ ከዩናይትድ ኪንግደም የተገኘ መረጃ የቤት ውስጥ ጥቃት ደርሶብናልና የሚል ሪፖርት 25 በመቶ እንደጨመረ ያመለክታል።

ወቅቱ የሰው ለሰው ግንኙነት እና ሥራም ሳይቀር ማኅበራዊ ሚዲያን የተመረኮዘ የሆነበትም ነው። ፕሮፌሰር ጃኩዊ እንደሚሉት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለቀቀው መረጃ ሥነ ልቦናዊ ጫና የሚያሳድርባቸው ሰዎች አሉ።

አንዳንዶች በቅንጡ ኩሽና ምግብ ሲያበስሉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ሲለጥፉ፤ ልጆቻቸውን ለመመገብ የተቸገሩ ሰዎች ስሜት እንደሚጎዳ እንደምሳሌ ይጠቅሳሉ። ''ሴቭ ዘ ችልድረን' የሠራው ጥናት የፕሮፌሰሯን ሀሳብ ያጠናክራል።

ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ምን እንደሚመግቡ፣ እንዴት በትምህርት ሊደግፏቸው እንደሚችሉም ያወጣሉ ያወርዳሉ። በአንጻሩ ልጆችም ከቤተሰባቸው አንዱ በበሽታው ሊያዝ ይችላል ብለው ይሰጋሉ። የምግብ እጥረትና ጓደኞቻቸውን አለማግኘትም ያሳስባቸዋል። ሰዎች እየተፈጠረ ባለው ነገር ላይ አንዳችም ቁጥጥር እንደሌላቸው ማወቃቸው ሌላው የጭንቀት ምክንያት ነው።

የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ዶ/ር ፑኒት ሳህ "የሰው ልጅ ነገሮችን መቆጣጠር ሲሳነው ለጭንቀት ይጋለጣል" ይላሉ። ይህን ጭንቀት ለማስተንፈስ አንዳንዶች የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲሠሩ፣ ሌሎች ደግሞ ቤት በማጽዳት እና አትክልት በመትከል ይጠመዳሉ።

ዶክተሯ እንደሚሉት፤ የአንድ ቤተሰብ አባላት ለሰዓታት አብሮ ለመሆን መገደዳቸው፤ ቤተሰባዊ ግንኙነታቸውን ሊቀይረው ይችላል። የቤተሰብ አባላት ከቀደመው ጊዜ በላቀ እርስ በእርስ የሚተዋወቁበትም ጊዜ ነው።

"ይሄ መስተጋብር መጥፎ ነው ብለን ማሰብ የለብንም" ይላሉ። ብዙዎች ጥሩ ስሜት የሚፈጥርላቸውን ነገር ለማግኘት እየሞከሩ ነው። አንዳንዶች ቤት ሆነው ሲሠሩ፤ የሥራ ቦታ ልብስ ማድረጋቸውን እንደምሳሌም ይጠቅሳሉ።

ትምህርት ቤቶች ስለተዘጉ ልጆች እንደ ዙም ባሉ ዘመነኛ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለመማር ተገደዋል።

በዚህ ወቅት ቤተሰቦች ልጆቻቸውን በትምህርት እንዲያግዙም ይጠበቃል። ሆኖም በርካታ ወላጆች ልጆቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ትምህረት እየሰጧቸው እንዳልሆነ ስለሚሰማቸው ይጨነቃሉ። ጥፋተኛነትም ይሰማቸዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ኃላፊ፤ "ቤተሰቦች አትጨነቁ፤ ማንም ጀብደኛ እንድትሆኑ አይጠብቅም" ሲሉ የማጽናኛ መልዕክት የላኩትም የቤተሰቦችን ጭንቀት ስላስተዋሉ ነበር።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ለሰላምታ እጃቸውን ከዘረጉ 10 ዓመት ያስቆጠሩት መምህር