ኮሮናቫይረስ በአሜሪካ ከነጮች ይልቅ በጥቁሮች ላይ ለምን ጨከነ?

አንዲት አፍሪካ አሜሪካዊት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ኮሮናቫይረስ ዘር፣ ቀለም፣ ሃብት፣ ጾታና ሃይማኖት አይለይም ይባላል። ታዲያ በአሜሪካ ከነጮች ይልቅ በጥቁሮች ላይ ምነው ክንዱ በረታ?

በቅርብ ከወደ አሜሪካ የወጡ መረጃዎች አስገራሚ ሆነዋል።

ይህ ዘገባ ሲጠናቀር በአሜሪካ 370 ሺህ ሰዎች በወረርሽኙ ተጠቅተዋል። 11ሺህ ሰዎች ደግሞ ሞተዋል። ከዚህ አሐዝ የጥቁሮች ድርሻ ከፍተኛ ነው።

ለምሳሌ ቺካጎን እንመልከት።

በቺካጎ ከጠቅላላው ነዋሪ የጥቁሮች ብዛት 30 ከመቶ ብቻ ነው። ወደ ኮሮናቫይረስ ስንመጣ ግን በቺካጎ ከሞቱት ሰዎች 70 ከመቶ ጥቁሮች ናቸው። በቫይረሱ ከተያዙት ደግሞ ግማሹ ጥቁሮች ናቸው።

ከኤፕሪል 5 ወዲህ ያለውን ቁጥር እንኳ ብንመለከት በቺካጎ 4ሺህ 680 ሰዎች ቫይረሱ ይዟቸዋል፡፡ 1824ቱ ጥቁሮች፣ 847ቱ ነጮች፣ 478 ሂስፓኒክ እና 126 ኢሲያዊ ዝርያ ያላቸው ናቸው።

ወደ ኢሊኖይ ግዛት እንሂድ። ተመሳሳይ ነገር እናገኛለን።

እዚያ የጥቁሮች ብዛት 14 ከመቶ ብቻ ነው። 41 ከመቶ ሟቾች ግን ጥቁሮች ሆነው ተገኝተዋል።

የቺካጎ የኅብረተሰብ ጤና ኮሚሽነር ዶ/ር አሊሰን በቺካጎ ጥቁሮች በኮሮና እያለቁ ነው ብለዋል። ማኅበራዊ ጥግግታቸው ከሆነ ብለን ወደ ሱቆቻቸው እየሄድን ይህንኑ ለመከታተል አስበናል ሲሉም አስታውቀዋል።

የቺካጎ ከንቲባ በበኩላቸው ጥቁሮች በሚበዙባቸው መጠጥ ቤቶች አካባቢ ሰዓት እላፊ ለማሳለፍ አስበናል ብለዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃስ ጥቁሮች በብዛት እየሞቱ ነው?

ሚቺጋን ሌላኛዋ ግዛት ናት። በሚቺጋን ከጠቅላላው ነዋሪ የጥቁሮች ብዛት 14 ከመቶ ብቻ ነው። በኮሮና ከሞቱት ውስጥ ግን 41 ከመቶ ጥቁሮች መሆናቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

በሚቺጋን በኮሮና የሞቱት ነጮች 28 ከመቶ ብቻ ናቸው።

በሚቺጋን ግዛት ውስጥ ትልቁ ከተማ ዴትሮይት ነው። በዚያ ከተማ በኮሮናቫይረስ ከተያዙት 80 ከመቶዎቹ ጥቁሮች መሆናቸው አስገራሚ ነው፡፡

በዊስኮንስን ግዛት ትልቁ ከተማ ሚልዎኪ ነው፡፡ በዚያ የጥቁሮች ብዛት 26 ከመቶ ብቻ ቢሆንም በኮሮና የሞቱት ጥቁሮች ግን 81 ከመቶ ሆነዋል፡፡

እነዚህን ከተሞች ናሙና ወሰድን እንጂ በመላው አገሪቱ ቁጥሮች ለጥቁሮች የበለጠ ሞትን አመልካች ሆነዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ባዷቸውን ከቀሩት የቺካጎ ጎዳናዎች አንዱ

ለምን ኮሮናቫይረስ በጥቁሮች ላይ ክንዱ በረታ?

የጤና ባለሞያዎች ነገሩ ሰፊ ጥናት እንደሚፈልግና በዚህ ደረጃ እንዲህ ነው፤ እንዲያ ነው ማለት እንደማያስፈልግ ከተናገሩ በኋላ የሚያነሷቸው መላምቶች ግን አሉ።

የጥቁሮች ማኅበራዊ ሕይወት በጥግግት ላይ የተመሰተ መሆኑ አንዱ ነው።

የኮሮናቫይረስ ቁጥርን ለመቀነስ ደግሞ መራራቅንና ራስን ማግለል እጅግ ወሳኝ ዘዴ ነው። ይህ ለጥቁሮች በቀላሉ የሚሳካ ነገር አይደለም። በብዙ ምክንያት. . . አንዱ ባሕል ነው፤ ሌላው ድህነት ያመጣው የአኗኗር ዘይቤ።

የማኅበረሰብ ጤና ባለሞያዎች ሌላ የሚያነሱት የጥቁሮች ጤና ሁኔታ ቀድሞስ ቢሆን መቼ በጎ ሆኖ ያውቃል የሚለውን ነው።

ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ ደም ግፊት እንዲሁም ስኳር ከብሔራዊ አማካይ ቁጥሩ በላይ ጥቁሮች የተጠቁባቸው በሽታዎች ናቸው።

የቺካጎ ከንቲባ እንደሚሉት ወትሮም ጥቁር ነዋሪዎቻችን ከነጮች ይልቅ በልብ ህመምና የመተንፈሻ አካላት ጤና መቃወስ የተጎዱ ሕዝቦች ነበሩ።

ኮሮናቫይረስ ደግሞ በሽታ ያለበት ሰው ላይ ይጨክናል።

ዶ/ር ካሜሮን ዌብ ቨርጂኒያን ወክለው ለኮንግረስ ወንበር የሚወዳደሩ አፍሪካ-አሜሪካዊ ናቸው። ምነው ኮሮናቫይረስ በጥቁሮች ላይ ጨከነ ተብለው ለተጠየቁት የመለሱት የሚከተለውን ነው።

"ወረርሽኙ ያጋለጠው ነገር ቢኖር በአሜሪካ የገቢ ልዩነትና የኑሮ ሁኔታ እንዴት በቀለም ላይ መሠረት እንዳደረገ መሆኑን ነው።"