ረመዳን ጾምና ሌሎች በዓላት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት

ኢፍጣር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ኢፍጣር

ረመዳን

የረመዳን ጾም ገብቷል። ይህ ወር በሙስሊሞች ዘንድ ቁርዓን ለነብዩ መሐመድ የተገለጠበት ጊዜ እንደሆነ ይታመናል።

በዚህ ወር በመላው ዓለም የሚገኙ ሙስሊሞች ቀን ቀን (ፀሐይ ወጥታ እስክትገባ) ከማንኛውም ምግብም ሆነ መጠጥ ራሳቸውን ያቅባሉ። ፈጣሪያቸውን ስለ ምሕረትና ይቅርታ ይለማመናሉ።

ሁልጊዜ ምሽት የዕለቱን ጾም ለመግደፍ ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ ተሰብስቦ ቴምር፣ ሳምቡሳና ሌሎች ምግቦችን ይቋደሳል። ከዚያ በኋላም ተራዊህ ተብሎ ለሚጠራው የደቦ ሶላት በርካታ ሰዎች ወደ መስጊድ ይተማሉ።

ይህ ግን በኮሮናቫይረስ ዘመን የሚታሰብ አይደለም።

በእንግሊዝ አንድ የሙስሊም ወጣቶች ማኅበር አለ። ሙስሊም ቴንት ፕሮጀክት ይባላል። የወቅቱን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት አዲስ ሐሳብ አፍልቋል።

ከዚህ ቀደም ወጣቶቹ በሎንዶን እንደ ትራፋልጋር ባሉ ሁነኛ አደባባዮች ድንኳን ጥለው የኢፍጣር መርሀ ግብር የዘጋጁ ነበር። ማንኛውም መንገደኛ ወደ ድንኳኑ ጎራ ብሎ ከገበታው መቋደስ ይችል ነበር።

በዚህ ዓመት ግን ይህ ሊሆን አይችልም፤ ኮሮናቫይረስ የሁሉም ዜጋ ቤት መቀመጥን ግድ ብሏል።

ከዚያ ይልቅ ወጣቶቹ የኢንተርኔት ኢፍጣርን እያሰቡ ነው። ዙም በተባለ የሞባይል መተግበሪያ በርካታ ሰዎች በስክሪን እየተያዩ ባሉበት ኢፍጣራቸውን የሚቋደሱበት ዘዴ ይሆናል ተብሏል።

የፀሐይ መጥለቂያ ጊዜ ጸሎት (መግሪብ) በኋላ ሰዎች ባሉበት ኢንተርኔታቸውን ከፍተው እየተጨዋወቱ በስክሪን እያወጉ አብረው ያሉ ያህል እየተሳሳቁ ያፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የ2009 ዓ.ም የስቅለት በዓል በቦሌ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን

በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው የዓለማችን ታላላቆቹ ሐይማኖቶች ከቀናት በኋላ ቀደም ሲል በርካቶችን በአንድ ቦታ ላይ የሚያሰባስቡ ሥነ ሥርዓቶችን የሚያከናውኑባቸው ጊዜያት እየተቃረቡ ነው።

ባለንበት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዘመን እነዚህ ሐይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች እንዴት ሊከናወኑ እንደሚችሉ የብዙዎች ስጋትና ጥያቄ ነው።

ፋሲካ

የፋሲካ በዓል ኢትዮጵያ ውስጥ በሚያዚያ 11 /2012 ዓ.ም ተከብሯል። በቀሪው ዓለም የሚገኙ ብዙዎቹ የክርስትና እምነት ተከታዮች ደግሞ ከአንድ ሳምንት ቀደም ብለው አክብረተውታል።

ይህ ቀን እየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ፣ ሞቶን ድል በማድረግ የተነሳበት ትንሳኤው የሚዘክርበት ነው።

አርብ የስቅለቱ ዕለት የስግደት ሥነ ሥርዓት ይካሄዳል። ምዕመኑ ወትሮ አቅራቢያው ወደሚገኝ ቤተክርስቲያን የሚተምበት ጊዜ ነበር። ይህ ግን በብዙ ቦታዎች የሚጠበቀው ሥነ ሥርዓት ዘንድሮ አልሆነም።

ከስቅለት በፊት ደግሞ ጸሎተ ሐሙስ አለ። ካህናት እግር ያጥባሉ፣ ቅዳሴም ይኖራል። ይህ ሁሉ በቤተክርስቲያን ውስጥ ምዕመናን በሚገኙበት ነበር የሚካሄደው። ይህ ዘንድሮ እንዴት ሊካሄድ ይችላል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

ከዚህ ሁሉ ቀደም ብሎ ማክፈል ሐሙስ ይጀምራል። ቅዳሜ ሌሊት 9፡00 ሰዓት ይፈሰካል።

እንዲያውም ያን ቀን ሌሊት ቤተክርስቲያን ነው የሚታደረው፤ ቅዳሜ-ሹር ሥነ ሥርዓትም መሰባሰብን ይፈልጋል። ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ የሚፈሰከው።

እነዚህ ሥነ ሥርዓቶች ከሞላ ጎደል የምዕመኑን በአንድ ቦታ መሰባሰብ የሚሹ ናቸው።

ይህ በኮሮናቫይረስ ዘመን የማይታሰብ ሊሆን ይችላል። ኬንያ ነገሩ ሁሉ በኢንተርኔነት ነው የሚፈጸመው።

ካሮሊ በናይኖቢ የምትኖት ክርስትና እምነት ተከታይ ናት። እነዚህን መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓቶች ዙም በተሰኘው የስልክ መተግበሪያ ነው የተከታተልነው ትላለች።

"በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ቅዳሜ ሌሊት ቁርባን የመቀበሉ ሥነ ሥርዓት በሐሳብ ነው ልንታደመው የምንችለው።"

ምንም እንኳ ኬንያ እንደ አንዳንድ አገሮች ሙሉ በሙሉ የሕዝብ እንቅስቃሴን ባትገድብም ምሽት ላይ ሰዓት እላፊን አውጃለች።

ከእኛ ቤተክርስቲያን ዙም በተሰኘው የመገናኛ ዘዴ በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እናደርጋለን። ጸሎትም የምናደርገው በዚያው መንገድ ነው ትላለች ካሮሊ።

ካሮሊ ይህ ባሉበት ሆኖ የመጸለዩ ነገር ምን ስሜት እንደፈጠረባት ስትናገር እንዲህ ትላለች።

"በአንድ በኩል ፈተና ነው። በሌላ በኩል ግን ባለንበት ወደ አምላካችን እንድንቀርብ፣ ጸሎትን ከምንወዳቸው ከልጆቻችን ጋር በቅርብ እንድንሳተፍ ዕድል ሰጥቶናል።"