ኢዘዲን ካሚል፡ ኮሮናቫይረስ ለመቆጣጠር የፈጠራ ሥራዎቹን ያበረከተው ወጣት

ኢዘዲን ካሚል እና የፈጠራ ሥራው

የፎቶው ባለመብት, Ezedin Kamil

ኢዘዲን ካሚል ይባላል። የ12ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ነው። እስካሁን ከትምህርት ሰዓት ውጭ 30 የሚሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን ጨምሮ 7 የሚሆኑ የአንድሮይድ መተግበሪያዎችንም እንደሰራ ይናገራል።

ከፈጠራ ሥራዎቹ ውስጥ ለ13ቱ የፈጠራ ሥራዎቹ ከ'ሴቭ አይዲያስ ኢንተርናሽናል' የባለቤትነት መብት እንዳገኘ ገልፆልናል።

የኮሮናቫይረስ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተረጋገጠ በኋላ ደግሞ ከጓደኛው ጋር በመሆን ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ ሁለት የፈጠራ ሥራዎችን ሰርቷል።

ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነ የእጅ መታጠቢያ

የእጅ መታጠቢያው ሙሉ በሙሉ ከእጅ ንክኪ የፀዳ ሲሆን፤ በተገጠመለት ሴንሰር የሰዎችን እንቅስቃሴ በመረዳት ያለ ንክኪ ፈሳሽ ሳሙና ጨምቆ በመስጠት ውሃውን ከፍቶ ያስታጥባል። መታጠቢያው መብራት በሚኖርበት ጊዜ በዚህም መልክ መጠቀም ያስችላል። የኤሌክትሪክ ኃይል ከተቋረጠ ወይም ከሌለስ? ኢዘድን ለዚህ መላ ዘይዷል።

ኢዘዲን እንደሚለው መብራት ሁልጊዜ አስተማማኝ ባለመሆኑና መታጠቢያውን ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል መንገድ ላይ ማስቀመጥ ከተፈለገ ሌላ አማራጭ ዘዴ መጠቀሙን ይገልጻል።

በእግር የሚረገጥ ፔዳል በመግጠም ከንክኪ በፀዳ መልኩ እጅን መታጠብ ያስችላል። ይህ የፈጠራ ሥራውም በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘለት ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, Ezedin Kamil

የምስሉ መግለጫ,

እስካሁን 35 የሚሆኑ ከእጅ ንክኪ ነፃ የእጅ መታጠበያዎች በወልቂጤ የተለያዩ ቦታዎች አገልግሎት እየሰጡ ነው።

መጀመሪያ ሥራውን ሲጀምሩ ወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ድጋፍ እንዳደረገላቸው የሚገልፀው ኢዘዲን፤ ጠቃሚ መሆኑ ከታመነበት በኋላ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በጋራ በመሆን 35 የሚሆኑ እጅ መታጠቢያዎችን አዛጋጅተዋል።

እነዚህን የእጅ መታጠቢያዎችም በወልቂጤ ከተማና በገብሪ ክፍለ ከተማ በተለይ ሰው የሚበዛባቸው፤ የባንክና ሆስፒታል መግቢያና መውጫ በሮች እንዲሁም ጤና ጣቢያዎች አካባቢ በማስቀመጥ ሰዎች እንዲገለገሉበት ተደርጓል።

የተለያዩ ግለሰቦችም የእጅ መታጠቢያው እንዲሰራላቸው ትዕዛዝ እንደሰጡ ኢዘዲን ገልፆልናል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ወጣት ኢዘዲን ካሚል ከሠራቸው የፈጠራ ሥራዎቹ አንዱ ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነ የእጅ መታጠቢያ ነው።

መካኒካል ቬንትሌር

ወረርሽኙን ተከትሎ እያጋጠመ ያለውን የቬንትሌተር እጥረት ችግር ለመፍታትም ሁለት ነገሮችን አስቦ ነበር።

አንደኛው ሜዴትሮኒክ የሚባል ህክምና እቃዎች የሚያመርት ካምፓኒ የለቀቀውን PB560 የተባለ ሞዴል ቬንትሌተር በመቅዳት በአገር ውስጥ ማምረት መቻል ሲሆን ሌላኛው የራሱን ፈጠራ የሆነ መካኒካል ቬንትሌተር መስራት ነው።

በመሆኑም በአገር ውስጥ በሚገኙ ቁሳቁሶች ሜካኒካል ቬንትሌተር መስራቱን ነግሮናል።

የህክምና እቃው ውድ መሆኑና አሁን ባለው ሁኔታ እጥረት መኖሩ ለፈጠራ ሥራው እንዳነሳሳው ይናገራል።

በመሆኑ በቀላል ዋጋ በብዛት ቢመረት መንግሥት በሃገሪቷ በብዛት ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ መዋል ይችላል ብሏል።

"እነዚህ እቃዎች ከውጭ ነው የሚገቡት" የሚለው ኢዘዲን እነርሱም ጋር የቫይረሱ ወረርሽኝ ከፍተኛ በመሆኑ እጥረት ስለሚያጋጥም አገር ውስጥ በሚገኙ እቃዎች ማምረት እንደሚቻል ለማሳየት የፈጠራ ሥራውን እንደሰራው ገልጾልናል።