ኮሮናቫይረስ፡ እንዴት ቱርክሜንስታን እስካሁን ምንም በኮሮና የተያዘ ሰው ሪፖርት አላደረገችም?

ብስክሌት የሚነዱ ስፖርተኞች

የፎቶው ባለመብት, MIGRATION.GOV.TM

የምስሉ መግለጫ,

የብስክሌት ውድድር

የኮቪድ-19 ስርጭት በመላው ዓለም እያደገ ቢሄድም እስካሁን በርካታ አገራት በቫይረሱ የተያዘ ሰው አላስመዘገቡም። ከእነዚህ መካከል ጨቋኝ መንግሥት ያላት ቱርክሜንስታን አንዷ ናት።

ብዙ ባለሙያዎች ግን ወረርሽኙን ለማስቆም የሚደረገውን ሙከራ ሊያስተጓጉል በሚችል መልኩ መንግሥት እውነትን እየደበቀ ሊሆን ይችላል በሚል ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

ዓለም ከኮሮናቫይረስ ጋር እየታገለ አንዳንድ አገራትም ዜጎቻቸው ከቤት እንዳይወጡ በሚያደርጉበት በአሁኑ ወቅት ቱርክሜንስታን ግን የዓለም ጤና ቀንን ለማክበር የብስክሌት ውድድር ማክሰኞ ዕለት አካሂዳለች ።

የመካከለኛው እስያዋ አገር በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው እንደሌለባት አስታውቃለች። ሆኖም ሳንሱር በማድረግ ታዋቂ በሆነው መንግሥት የቀረበውን አሃዝ ማመን እንችላለን?

"ከቱርክሜንስታን የተገኘው መረጃ በግልፅ የማይታመን ነው" ሲሉ የአገሪቱን የጤና አጠባበቅ ሥርዓትን ያጠኑት በለንደን የሃይጂንና ትሮፒካል ሜዲሲን ትምህርት ቤት ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ማርቲን ማኪ ተናግረዋል።

"በማይታመን መልኩ ላለፉት አስር ዓመታት ከኤችአይቪ /ኤድስ ጋር የሚኖሩ ሰዎች እንደሌሉ ገልጸዋል። በፈረንጆቹ በ 2000ዎቹ የተለያዩ ወረርሽኞችን መረጃ ሲደብቁ ኖረዋል" ይላሉ።

ብዙዎች በቱርክሜንስታን የኮቪድ -19 ከወዲሁ ሊኖር ይችላል ብለው ይፈራሉ።

"በመንግሥት ድርጅት ውስጥ የሚሠራው ባልደረባዬ ቫይረሱ እዚህ አለ ወይም ሰምቻለሁ አትበል። ካልሆነ ግን ችግር ውስጥ እገባለሁ ብሎኛል" ሲሉ ማንነታቸው እንዳይገለጽ የሚፈልጉ የዋና ከተማዋ አሽጋባት ነዋሪ አስታውቀዋል።

ቱርክሜንስታን አብዛኛዎቹን የድንበር መግቢያዎቿን ከዘጋች ግን ከአንድ ወር በላይ ሆናት።

ከየካቲት መጀመሪያ ጀምሮ ወደ ቻይናና ወደ ሌሎች አገሮች የሚደረጉ በረራዎችን የሰረዙ ሲሆን ሁሉንም ዓለም አቀፍ በረራዎች ከመዲናዋ ለይቶ ማቆያ ወደ ተቋቋመበት እና በሰሜን-ምሥራቅ ወደምትገኘው ቱርሜንባባት አዙራለች።

ሆኖም እንደ ነዋሪዎች ገለፃ አንዳንዶች ከለይቶ ማቆያው እጅ መንሻ እሰጡ በመውጣት ለሁለት ሳምንት ያህል በድንኳን ውስጥ ላለመኖር ወስነዋል።

ወደ አገሪቱ የሚገቡ እና ምልክቶችን የሚያሳዩ ሁሉ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው። ሆኖም በቀን ምን ያህል ምርመራዎች እንደተካሄዱ እና አገሪቱ በአጠቃላይ ስንት መመርመሪያ መሳሪያዎች እንዳሏት ትክክለኛ ቁጥር ለመስጠት አልተቻለም።

ኮሮና
Banner

ይሁን እንጂ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በሽታን ለመቋቋም የጤና ሥርዓቱ ምን ያህል ዝግጁ ነው?

"አናውቅም። እኛ የተወሰነ ዝግጁነት ደረጃ እንዳላቸው ተነግሮናል። እኛም አንጠራጠርም… ምክንያቱም ሆስፒታሎች የተሟሉ በመሆናቸው" ብለዋል ሲሉ በአገሪቱ ያሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይ ተናግረዋል።

ጨምረውም "ወረርሽኝ ከተከሰተ ግን እንደማንኛውም አገር በጤናው ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል። ለዚህም ነው ምንም ያህል ቢዘጋጁ (አብዛኛውን ጊዜ በቂ አይደለም) ተጨማሪ መሣሪያዎችን እንዲገዙ እያግባባን ነው።"

ሕዝቡ ስለተከሰተው ወረርሽኝ ግንዛቤ ግንዛቤ አለው። በከተሞች መካከል የሚደረግ እንቅስቃሴ የተከለከለ ሲሆን ወደ አሽጋባት የገቡ ሰዎች ለመንቀሳቀስ የሐኪም ፈቃድ ያስፈልጋቸዋል።

ገበያዎች እና መስሪያ ቤቶች ዩዛርሊክ በተሰኘ የሳር ዓይነት እንዲታጠኑ እየተደረገ ነው። ምንም እንኳን ማስረጃ ባይኖርም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጉርባንጉሊ ቤርዲሙክሃሜዶቭ ዕጽዋቱን ማቃጠል ቫይረሱን እንደሚዋጋ አስታውቀዋል።

ከአብዛኛው ዓለም በተቃራኒ ቱርክሜኒስታን ውስጥ የዕለት ተዕለት ኑሮ በመደበኛነት ቀጥሏል።

ካፌዎች እና ምግብ ቤቶች ክፍት ናቸው። ብዙ ሰዎች ለሠርግ ይሰበሰባሉ። ጭምብል የሚያደርጉ ሰዎች ካለመኖራቸውም በላይ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸው ዝግጅቶች ቀጥለዋል።

ኮሮናቫይረስ ያመጣውን ስጋት ለመቀበል ሀገሪቱ እየተቸገረች እንደሆነ ያሳያል።

ለምን ሊሆን ይችላል? የዓለም የጤና ቀንን ለማክበር የተደረገው የብስክሌት ውድድር ማብራሪያ ሊሰጥ ይችላል።

ፕሬዝዳንት ጉርባንጉሊ ቤርዲሙክሃሜዶቭ ኮከብ እና የዓመታዊው ዝግጅት ዋናው ትኩረት ነበሩ።

የጤናማ አኗኗር ምስል ተደርገውም ይወሰዳሉ። መንግሥት ቴሌቪዥን በመደበኛነት በጂም ውስጥ ክብደትን ሲያነሱ ወይም ብስክሌት ሲነዱ በተደጋጋሚ ያሳያል።

መሳሳይ ዩኒፎርም የለበሱ የመንግሥት ሠራተኞች የጠዋት ስፖርታዊ ልምምዶቻቸውን የሚያካሂዱበት የ"ጤና እና ደስታ" ዘመቻ አንቀሳቃሽም ናቸው።

የእነዚህ ሁሉ ዋና መልዕክት ምስጋና ለፕሬዚዳንቱ አገሪቱ ጤናማ እና ደስተኛ መሆኗን ለማሳየት ነው።

ፕሬዝዳንት ጉርባንጉሊ ቤርዲሙክሃሜዶቭ የስልጣን ዘመናቸውን "የኃይል እና የደስታ ዘመን" ሲሉ አውጀዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መልዕክቶቹ ምን ያህል እንዳልተሳኩ ሊያጋልጥ ይችላል። በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል መንግሥት ምንም እንኳን ዜጎቹ በበሽታው ቢያዙም ወረርሽኙን ለመደበቅ የሚሞክረው።

ይህ ነው ፕሮፌሰር ማኪን ያስጨነቀው "ኮቪድ-19 በፍጥነት ከቻይና ወደ ተቀረው ዓለም እንዴት እንደተዳረሰ አይተናል። አሁን በምንኖርበት ዓለም ሁሉም አገር እኩል በሚባል ደረጃ ተጋላጭ ነው" ብለዋል።

"አንዳንድ ሃገራት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ቢችሉም፤ በሌሎች አገራት የመቀጠል አደጋ አለው። ቱርክሜኒስታንም ሌላ ምሳሌ ልትሆን ትችላለች።"