የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለአምስት ወራት በመላው አገሪቱ ተግባራዊ ይሆናል ተባለ

ጠቅላይ አቃቤ ህግ

የፎቶው ባለመብት, Attoreny General

ኢትዮጵያ እየተስፋፋ ያለውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ያወጠችው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለአምስት ወራት ተግባራዊ እንደሚሆን ተገለጸ።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባወጣው ዝርዝር ማብራሪያ ላይ እንዳመለከተው ውሳኔው በመላው አገሪቱ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን የሚወሰዱ እርምጃዎችን በዝርዝር ከማስቀመጥ ተቆጥቧል።

ለዚህም በሰጠው ማብራሪያ ላይ "ዝርዝር እና ቋሚ የመብት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን ከመዘርዘር ይልቅ እንዳስፈላጊነቱ ተለዋዋጭ በሆነ ሁኔታ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በማውጣት እገዳዎችን እና እርምጃዎችን እንዲደነግግ" አዋጁ ስልጣን እንደሰጠ አመልክቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማስፈጸም ኃላፊነትን በተመለከተ የሚኖሩ የመብት እገዳዎችና እርምጃዎችን ዝርዝር ሁኔታ በየጊዜው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለዚሁ ዓላማ በሚያቋቁመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ እየተወሰነ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል።

ስለዚህም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስር ማንኛውም ሰው በሕግ አስከባሪ አካላት ወይም ሌላ በሕግ ሥልጣን ባለው አካል የሚሠጥ ሕጋዊ ትዕዛዝ እና መመሪያን የመፈጸም ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል።

በተጨማሪም የፌደራልና የክልል የሕግ አስከባሪ ተቋማትና ሌሎች በሕግ ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት ተመጣጣኝ ኃይል በመጠቀም በአዋጁ መሰረት ይፋ የተደረጉ የመብት እገዳዎችንና እርምጃዎችን የማስፈጸም ስልጣን ተሰጥቷቸዋል።

ስለዚህም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተደነገጉ የመብት እገዳዎችን፣ እርምጃዎችን፣ የተሰጠ መመሪያ ወይም ትዕዛዝን ሆን ብሎ የጣሰ ማንኛውም ሰው እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከአንድ ሺህ ብር እስከ ሁለት መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ሊቀጣ እንደሚችል ያስቀምጣል።

ይህ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ በኩል ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የወጣው ማብራሪያ እንደጠቀሰው አዋጁ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት በሚፈቅደው መሰረት ለአገርና ለሕዝብ ደኅንንት አደጋ የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ የሚያስችለውን በአንቀጽ መሰረት አድርጎ ነው ብሏል።