የቢል ክሊንተንና የሞኒካ ሊዊንስኪን ቅሌት ያጋለጠችው ሴት ሞተች

ሊንዳ ትሪፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ሊንዳ ትሪፕ

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተንን በስልጣን ላይ እያሉ ከተከሰሱ ጥቂት የአገሪቱ መሪዎች መካከል እንዲገቡ ያደረገቻቸው ግለሰብ አረፈች።

በ90ዎቹ መጨረሻ የፕሬዝዳንት ክሊንተን ከትዳራቸው ውጭ ከዋይት ሐውስ አንዲት ሠራተኛ ጋር የድብቅ ፍቅር መጀመራቸውንና አንሶላ መጋፈፋቸውን ከጓደኛዋ ሞኒካ ሰምታ ክሊንተን እንዲከሰሱ መረጃ ያቀበለችው ሴት በ70 ዓመቷ ነው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው።

ሴትየዋን ለሞት ያበቃት ኮሮናቫይረስ ሳይሆን የጣፊያ ካንሰር ነው ተብሏል።

ሊንዳ ትሪፕ ከሞኒካ ሊዊኒስኪ ጋር የእድሜ አቻ ባትሆንም የቅርብ ወዳጇ ነበረች።

ያን ጊዜ እሷ በፔንታገን የመንግሥት ሠራተኛ የነበረች ሲሆን ሞኒካ ከክሊንተን ጋር ግንኙነት መጀመሯን ከነገረቻት በኋላ አብዛኛውን ንግግሯን በድብቅ በድምጽ ስትቀዳ ቆይታለች።

የቀዳቻቸውን ድምጾች ለመርማሪዎች አሳልፋ በመስጠቷ ክሊንተር ፕሬዝዳንትነታቸው ሊያጡ የደረሱበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር።

ሚስ ሊንዳ ትሪፕ የቢል ክሊንተር የወንድ ፈሳሽ በሞኒካ ሊዊንስኪ ሰማያዊ ቀሚስ ላይ መታየቱን ሁሉ በመጥቀስ ቢል ክሊንተን ከትዳራቸው ውጭ ስለመማገጣቸው በማያሻማ ሁኔታ መረጃ ይዛ ነበር።

ሊንዳ የያኔዋን ጓደኛዋን የሞኒካ ሊዊንስኪን ምስጢር አሳልፋ በመስጠቷ አንዳንዶች ቢያወግዟትም እሷ ግን በአርበኝነት ለአገሬ ያደረኩት ነገር ነው ስትል ቆይታለች።

ክሊንተር ክሳቸውን ሴኔት ካቋረጠው በኋላ ሊንዳ ከፔንታገን ተባረረች፤ ከዚያም በቨርጂኒያ ከባሏ ጋር አንዲት ሱቅ ከፍታ ትኖር ነበር።

ሊንዳ ከመሞቷ በፊት ሞኒካ ሊዊንስኪ በትዊተር ሰሌዳዋ፤ "ምንም እንኳ ያለፈው ታሪካችን መልካም ባይሆንም ለወ/ሮ ሊንዳ ጤንነት እመኛለሁ" ብላ ነበር።

በ1998 በሴኔት ፊት ቀርባ ምስክርነት የሰጠችው ሞኒካ ሊዊንስኪ የምስክርነት ቃሏን ስታሳርግ "ስለሆነው ነገር አዝናለሁ፤ ጓደኛዬ የነበረችው ሊንዳ ግን እጅግ እስጠሊታ ሴት ናት" ብላ ነበር።