ታይዋን ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም ላቀረቡት ክስ ምላሽ ሰጠች

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የታይዋን ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ዶክተር ቴድሮስ ትናንት የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ የቀረበው ዘረኝነትን መሰረት ያደረገ ክስ መሰረተ ቢስ ነው ሲል ተቃወመ።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ የግድያ ዛቻ እንደደረሰባቸውና ዘረኛና ጸያፍ ስድቦችን ሳይቀር እያስተናገዱ እንደሆነ ለዓለም ሚዲያ መናገራቸውን ተከትሎ ታይዋን ኃላፊው ይቅርታ ሊጠይቁኝ ይገባል ማለቷ ተዘግቧል።

ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም የግድያ ዛቻና የዘረኛ ንግግር ጥቃት እየተሰነዘረባቸው መሆኑን የተናገሩ ሲሆን "ከሁለትና ከሦስት ወር በላይ ዘረኛ ጥቃቶች ተሰንዝረውብኛል። ጥቁር፣ ባርያ ተብያለሁ። እውነቱን ለመናገር እኔ በጥቁርነቴ እኮራለሁ። የሚባለው ነገርም ግድ አይሰጠኝም" ብለዋል።

ቻይና እንደ እራሷ ግዛት ስለምትመለከታትና በዓለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ እውቅና እንዳታገኝ በምታሳርፈው ተጽእኖ ምክንያት የዓለም ጤና ድርጅት አባል ያልሆነችው ታይዋን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ከድርጅቱ አስፈላጊውን መረጃ አላገኘሁም በሚል ወቀሳ ስትሰነዝር ቆይታለች።

በዶ/ር ቴድሮስ ትናንት በሰጡት መግለጫ ላይ የዘረኝነት ቃላት እንደተሰነዘረባቸው የተናገሩ ሲሆን ይህም ከታይዋን በኩል እንደሆ ማመልከታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

"ሰውየው ያሉት ነገር መሠረተ ቢስ ነው፤ ታይዋን ምራቋን የዋጠች፣ የሰለጠነችና ተራማጅ አገር ናት፤ እንዲህ ዓይነት ነገር ውስጥ አትገባም" ብላለች ታይዋን፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል የወጣ መግለጫ።

የታይዋን 23 ሚሊዮን ሕዝብ በዓለም ጤና ድርጅት የተተበተበ ፖለቲካ ምክንያት ጉዳት ደርሶበታል ሲልም መግለጫው ጠቅሷል።

የዶ/ር ቴድሮስ በታይዋን ላይ የሰነዘሩት ክስ መሰረተ ቢስ ብቻ ሳይሆን ቅዠትም ጭምር ነው ያለው የታይዋን መግለጫ ለዚህ ኃላፊትነት ለጎደለው አነጋገር ሰውየው በአፋጣኝና በይፋ ይቅርታ ሊጠይቁን ይገባል ብለዋል።

ታይዋን ቫይረሱን መቆጣጠር ከቻሉ ጥቂት አገራት የምትመደብ ናት። በበሽታው የተያዙባት ሰዎች ብዛት 379 ሲሆን ሟቾች 5 ብቻ ናቸው።

ታይዋን የዓለም ጤና ድርጅት ቫይረሱ በተከሰተበት የሰጠሁትን የጥንቃቄ መረጃ ቸል ብሎታል ስትል ትከሳለች።