ሮናልዲንሆ በ800 ሺህ ዶላር ዋስ ሆቴል ውስጥ እንዲታሠር ታዘዘ

ሮናልዲንሆ
የምስሉ መግለጫ,

ሮናልዲንሆ

ብራዚላዊው የእግር ኳስ ጠቢብ ሮናልዲንሆ ጎቹ ፓራጓይ ከሚገኘው እሥር ቤት ተለቆ ውሳኔ እስኪሰጠው ድረስ ሆቴል ውስጥ እንዲሰነብት ታዟል።

ሮናልዲንሆና ወንድሙ ፓራጓይ ውስጥ ሃሰተኛ ፓስፖርትና ሌሎች ሰነዶች ይዘው ተገኝተዋል በሚል በፖሊስ ተይዘው ከአንድ ወር በላይ እሥር ቤት ውስጥ መሰንበታቸው አይዘነጋም።

ወንድማማቾቹ ከዚህ በፊት እንዲለቀቁ ይግባኝ ቢያመለክቱም ሰሚ ጠፍቶ ነበር። አሁን ግን እያንዳንዳቸው 800 ሺህ ዶላር ዋስ ጠርተው የፓራጓይ ዋና ከተማ አሱንሲዮን የሚገኝ ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ውስጥ እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተላልፏል።

የ40 ዓመቱ የእግር ኳስ ሰው ሮናልዲንሆና ወንድሙ አሲስ እኛ ሃሰተኛ ሰነድ መሆኑን አላወቅንም ነበር ሲሉ ይሟገታሉ። ጠበቃቸውም የወንድማማቾቹ እሥር ሕገ-ወጥ ነው ሲል ይከራከራል።

ውሳኔውን ያስተላለፉት ዳኛ ገንዘቡ ጫን ያለ እንዲሆን የተደረገው ግለሰቦቹ ሃገር ጥለው እንዳይጠፉ በማሰብ ነው ብለዋል።

ሮናልዲንሆ ወደ ፓራጓይ አቅንቶ የነበረው መፅሐፉን ለማስተዋወቅና አቅመ ደካማ ሕፃናትን የሚረዳ ድርጅትን ለመደገፍ ነው ተብሏል።

ሮናልዲንሆ የ2005 ባለንደኦር [የዓለም ኮከብ ተጫዋች ሽልማት] አሸናፊ ነበር። አልፎም በግሪጎሪ አቆጣጠር 2002 ከብራዚል ብሔራዊ ቡድን ጋር የዓለም ዋንጫን ማንሳት ችሏል።

ተጫዋቾቹ በኮከብነት ዘመኑ ለስፔኑ ባርሴሎና፣ ለጣልያኑ ክለብ ኤሲ-ሚላንና ለፈረንሳዩ ፒኤስጂ ተጫዋቷል። የእግር ኳስ ዕድሜው ሲጃጅ ደግሞ ወደ ትውልድ ሃገሩ ብራዚል በማቅናት ጫማዬን ሰቅያለሁ ሲል የዛሬ አምስት ዓመት ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም።