ኮሮናቫይረስ፡ ድብደባ፣ ግድያ፣ ስለላ በአፍሪካ

የኡጋንዳ ፖሊሶች የጎዳና ቸርቻሪዎችን ደብድበዋል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

የኡጋንዳ ፖሊሶች የጎዳና ቸርቻሪዎችን ደብድበዋል

ኮሮናቫይረስ መላው ዓለምን አስጨንቋል። መንግሥታት በረራ በማቆም፣ እንቅስቃሴ በመግታትም ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እየሞከሩ ነው።

አፍሪካ ውስጥ እነዚህን እርምጃዎች የሚያስፈጽሙት ፖሊሶች ዜጎችን ሲዘልፉ፣ ሲደበድቡ ገፋ ሲልም ሲገድሉ ታይቷል። ይህ የጸጥታ ኃይሎች ድርጊት፤ ማኅበረሰቡን ከኮሮናቫይረስ ለመጠበቅ የሚደረገው ጥረት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ወደመጋፋት እያመራ ይሆን? የሚል ጥያቄ አጭሯል።

በአፍሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሺህ በልጧል። መንግሥታት ወረርሽኙን ለመግታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየደነገጉ፣ የነዋሪዎችን እንቅስቃሴ እየሰለሉም ነው።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፤ እነዚህ እርምጃዎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት መሆኑን ካቆመ በኋላም ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ይሰጋሉ።

መንግሥታት የሰዓት እላፊ ገደብ መጣልና እንቅስቃሴ መግታት የሰዎችን ሕይወት ይታደጋል ይላሉ። ነገር ግን ተገቢ ያልሆነ ኃይል መጠቀምም የሰውን ሕይወት ይቀጥፋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ,

የኬንያ ፖሊሶች በምሽት ሲጓዝ ያገኙትን ወጣት ሲያስቆሙ

ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ውስጥ ለአምስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተደነገገው ትላንት ነበር። ነሐሴ ላይ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው አገራዊ ምርጫም ተራዝሟል።

ሆኖም ግን ምርጫው እንዲራዘም ከመወሰኑ በፊት ከተቃዋሚዎች ጋር ውይይት መደረግ ነበረበት ሲሉ የተቹ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ነበሩ።

የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያላግባብ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል የሚል ፍርሀት እንዳለው አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ፤ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በተመለከተ ከተቃዋሚዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄው አቶ ጣሂር መሐመድ፤ አዋጁ ዝርዝር መረጃ የለውም ብለዋል። "ዜጎች ምን እንደሚፈቀድና ምን እንደተከለከለ የማወቅ መብት አላቸው" ሲሉም አስረድተዋል።

የሚተላፉት ውሳኔዎች ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ያለሙ ናቸው ሲሉም አቶ ጣሂር ተችተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጋለች

ኬንያ

ኬንያ፣ ናይሮቢ ውስጥ በቤቱ በረንዳ ላይ ይጫወት የነበረ የ13 ዓመት ታዳጊ 'በባረቀ' የፖሊስ ጥይት ሕይወቱ አልፏል። በፖሊስ ተደብድቦ የሞተ የሞተር ሳይክል ነጂን ጨምሮ ሦስት ሌሎች ሰዎችም ሕይወታቸውን ማጣታቸውም ተዘግቧል።

ፕሬዘዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ስለተፈጠረው ነገር ኬንያውያንን ይቅርታ ጠይቀው፤ ማኅበረሰቡ ከፖሊስ ጋር እንዲተባበር ጠይቀዋል።

ኡጋንዳ

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ 'ሂውማን ራይትስ ዋች' በኡጋንዳ ፖሊሶች አላስፈላጊ ኃይል እየተጠቀሙ ነው ሲል ወንጅሏል።

ፖሊሶች አትክልት ቸርቻሪዎችን እና የታክሲ ሾፌሮችንም ደብድበዋል ተብሏል። በተጨማሪም ለቤት አልባ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎች የተዘጋጀ መጠለያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ 23 ሰዎችን ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሏል።

በተጨማሪም፤ እንቅስቃሴ መግታት በኡጋንዳ ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ ዘገባ የሠሩ አስር ጋዜጠኞች በፖሊስ መደብደባቸውን የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪው 'ሂውማን ራይትስ ኔትወርክ ፎር ጆርናሊስትስ' ለቢቢሲ ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

የደቡብ አፍሪካ ፖሊሶች የፕላስቲክ ጥይት ተኩሰዋል

መንግሥት፤ ቤት የሌላቸው ሰዎችን፣ የጎዳና ቸርቻሪዎችን እንዲሁም ሌሎችም ተጋላጭ የማኅበረሰቡ አባላትን መጠበቅ እንደሚገባው 'ሂውማን ራይትስ ዋች' ተናግሯል።

ባለፈው ማክሰኞ አስር የኡጋንዳ ፖሊሶች 38 ሴቶችን በለአንጋ በመግረፍና ጭቃ ውስጥ እንዲዋኙ በማስገደድ ተከሰዋል።

ደቡብ አፍሪካ

ደቡብ አፍሪካ ከመላው አህጉሪቱ በበለጠ በኮሮናቫይረስ የተያዙ በርካታ ሰዎች ያሉባት አገር ናት።

በአገሪቱ እንቅስቃሴ እንዲገደብ ከተወሰነ በኋላ ቢያንስ ስምንት ሰዎች እንደተገደሉ የደቡብ አፍሪካው ገለልተኛ መርማሪ ቡድን 'ኢንዲፔንደንት ፖሊስ ኢንቨስትጌቲቭ ዳይሬክቶሬት' አስታውቋል።

ኮሮናቫይረስ በተለይም ጠንካራ የጤና ሥርዓት ለሌላት አፍሪካ እጅግ አስጊ ነው። ሆኖም ግን ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች 'ፍሪደም ሀውስ' የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ሰብዓዊ መብትን እንዳይጋፉ እሰጋለሁ ብሏል።

ጋና

የጋና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፤ ለአገሪቱ ፕሬዘዳንት እንቅስቃሴን መግታት የሚያስችለው አዲስ ሕግ እንደሚያሰጋቸው ተናግረዋል።

ተቃዋሚ ፖለቲከኛው ራስ ሙባረክ "ፕሬዘዳንቱ ሕገ መንግሥቱ ላይ ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌ ተጠቅመው፤ በየሦስት ወሩ ፓርላማ እየመጡ፤ የድንጋጌውን አስፈላጊነት ለሕዝብ እንደራሴዎች እንዲያቀርቡ ነበር የምንፈልገው" ብለዋል።

አዲሱ ሕግ ግን ፕሬዝዳንቱ የሰዎችን እንቅስቃሴ እንዳሻቸው እንዲገድቡ ይፈቅዳል።

የአገሪቱ የፍትሕ ሚንስትር በበኩላቸው ሕጉ የዜጎችን ጤና እንደሚያስጠብቅ ይገልጻሉ።

ማላዊ

የማላዊ ፕሬዝዳንት ፒተር ሙታሪካ፤ ኮሮናቫይረስን "በፖለቲካው የሠሯቸውን ስህተቶች ለማረም" እየተጠቀሙበት ነው የሚል ትችት ቀርቦባቸዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መሪው ጊፍት ትራፔንስ እንደሚሉት፤ "መንግሥት ኮሮናቫይረስን ሥልጣኑን ለማራዘም ሊጠቀምበት ይፈልጋል።" የአገሪቱ የመረጃ ሚንስትር ማርክ ቦቶሚኒ ግን ክሱን አጣጥለዋል።

ከወራት በኋላ ምርጫ የሚጠብቃቸው ፕሬዝዳንቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግገዋል።

ታንዛንያ

ሦስት የታንዛንያ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች መንግሥት ኮሮናቫይስን ለመከላከለ እየወሰደ ስላለው እርምጃ "ሐሰተኛና የተሳሳተ መረጃ አስተላልፋችኋል" በሚል ተቀጥተዋል።

ስለቅጣቱ ዝርዝር መረጃ በመንግሥት ባይሰጥም፤ ጣቢያዎቹ ፕሬዘዳንት ጆን ማጉፉሊን ስለተቹ እንደተቀጡ እየተነገረ ነው። ፕሬዝዳንቱ "ኮሮናቫይረስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አይኖርም" ብለው ከተናገሩ በኋላ ቤተ ክርስቲያኖች አይዘጉ ማለታቸው ይታወሳል።

የስልክ ስለላ

ሌላው የመብት ተሟጋቾች ስጋት መንግሥት ዜጎችን የመሰለሉ ጉዳይ ነው።

የኬንያ መንግሥት ኮሮናቫይረስ አለባቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎችን በስልካቸው እየተከታተለ ነው። ቃል አቀባዩ ሳይረስ ኦጉና ክትትሉ ለ14 ቀን በለይቶ ማቆያ መሆን ያለባቸውን ሰዎች ለመጠበቅ የሚደረግ ነው ብለዋል።

ጠበቃና የግል መረጃ ጥበቃ ባለሙያ ሙጋምቢ ላይቡታ በበኩላቸው፤ ዜጎች ክትትል እየተደረገባቸው ስለመሆኑ መረጃ ሊሰጣቸው ይገባል ይላሉ።

ደቡብ አፍሪካ ከቴሌኮም ድርጅቶች ጋር በመተባበር ኮሮናቫይረስ ካለባቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ዜጎች የት እንደሄዱ ለማወቅ መረጃ እየሰበሰበሰች ነው።

በተባበሩት መንግሥታት የነፃነትና መብት ወኪል ዴቪድ ካይ እንደሚሉት፤ መሰል የጤና ቀውሶች ሲከሰቱ፤ መንግሥታት የተለያዩ የአደጋ ጊዜ እርምጃዎች መውሰዳቸው የተለመደ ነው።

"ከህክምና ጋር የተያያዘ ስለላ (ሜዲካል ሰርቬለንስ) እንደሚካሄድ እርግጥ ነው" ይላሉ።

ሆኖም ግን እርምጃዎቹ ሕግ ወጥ እንዳይሆኑ ቁጥጥር ሊደረግ እንደሚገባ ያስረዳሉ። ኮሮናቫይረስ ስጋት መሆኑ ሲቆም፤ እርምጃዎቹም መቆም እንዳለባቸውም ይገልጻሉ።

በዚህ ረገድ፤ ደቡብ አፍሪካ አንድ የቀድሞ ዳኛ መረጃ የመሰብሰብ ሂደቱን እንዲከታተሉና ሊስተካከል ይገባዋል የሚሉትን እንዲጠቁሙ መሾሟን የመብት ተሟጋቾች አወድሰዋል።