በድህረ-ኮሮና ዘመን በዓለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ድሃ ይሆናሉ

የኢንዶኔዥያ አርሶ አደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የኢንዶኔዥያ አርሶ አደሮች

የዚህ ቫይረስ ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት ገና ተሰፍሮ አላለቀም፡፡ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ባወጣው አንድ ሪፖርት እንዳለው ቢያንስ ግማሽ ቢሊዮን ሰዎች ወደ ድህነት ይወረወራሉ፡፡

ይህ ማለት ድህነት በዓለም ላይ በዚህ ደረጃ ሲጨምር ከ30 ዓመት በኋላ ይህ የመጀመርያው ይሆናል፡፡

ይህ አስደንጋጭ ሪፖርት የወጣው የዓለም ባንክ፣ የዓለማቀፉ የገንዘብ ፈንድ እና የጂ-20 ብልጹግ አገራት ሚኒስትሮች በአንድ ተሰብስበው ለመምከር ሳምንት ሲቀራቸው ነው፡፡

የአውስትራሊ ናሽናል ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ ክሪስቶፈር ሆሊ እንደሚሉት ኮቪድ-19 ከሚያመጣው የጤና ቀውስ የበለጠ የምጣኔ ቀውስ ይከሰታል፡፡

ይህ ጥንቅር በዓለም ከ4መቶ እስከ 6መቶ ሚሊዮን ሰዎች ሙልጭ ያለ ድህነትን ይቀላቀላሉ ይላል፡፡

ይህም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘላቂ የልማት ግብ ደንቃራ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ዘላቂ የልማት ግብ በ2030 ድህነትን ለማጥፋት ያለመ ነበር፡፡

‹‹የምርምር ውጤታችን እንደሚያሳየው በታዳጊ አገራት በአስቸኳይና በአስደናቂ ፍጥነት የድህነት ሴፍትኔት ካልተዘረጋ ኋላ ጉድ ነው የሚፈላው›› ይላሉ የኪንግስ ኮሌጅ ባልደረባ ፐሮፌሰር አንዲ ሰምነር፡፡

ይህ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚገድለውን ገድሎ፣ የሚያጠፋውን ጥፋት አድርሶ ዓለም ወደ ተለመደው የኑሮ ምህዋሯ ስትመለስ 7.8 ቢሊዮን የሚገመተው የዓለም ሕዝብ ግማሹ እልም ወዳለ ድህነት እንደሚገባ ጥናቱ ይተነብያል፡፡

ከዚህ ውስጥ 40 ከመቶው አዲስ ድህ ቤቱ በምሥራቅ ኢሲያና ፓስፊክ ሲሆን አንድ ሦስተኛው ደግሞ በሰሀራ በታች በሚገኙ አገራትና በደቡብ ኢሲያ ይሆናል፡፡

በዚህ ሳምንት መጨረሻ 100 የሚሆኑ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች የድሀ አገራት እዳ በአስቸኳይ እንዲሰረዝ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ይህም በድምሩ 25 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል፡፡