በጥርስ ሕመም የሚሰቃዩ እንግሊዛዊያን የሐኪም ያለህ እያሉ ነው

የጥር ሐኪም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በእንግሊዝ በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ጥርሳቸውን ታመው ነገር ግን ሐኪም ማየት አልቻሉም።

የብሪታኒያ የጥርስ ሐኪሞች ማኅበር ለቢቢሲ እንደተናገረው በአገሪቱ የጥርስ ሐኪሞች ከታማሚዎች በሚደወሉ የጥርስ ጥሪዎች ተጨናንቀዋል። ምን ማድረግ እንዳለባቸውም ግራ ገብቷቸዋል።

ለመታከም ለምን አልቻሉም?

በዚህ ሰዓት በመላው እንግሊዝ ሁሉም የጥርስ ሕክምናዎች ቆመዋል። በተለይ የመደበኛ የጥርስ ቼክአፕ ምርመራ እንዲቆም የተደረገው ከማርች 20 ጀምሮ ነበር።

ይህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው የኮሮናቫይረስን ሥርጭት ለመግታት በሚል ነው።

እጅግ አጣዳፊ የጥርስ ሕክምናን ለሚሹ ግን የእንግሊዝ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት አጣዳፊ የጥርስ ሕክምና ማዕከላትን እያቋቋመ ነው።

ነገር ግን እነዚህ በቁጥር ትንሽ ናቸው። በዚያ ላይ አገልግሎታቸው ሊዳረስ አልቻለም።

በርካታ ሰዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ምንም እንኳ በማያቆም የጥርስ ስቃይ ላይ ቢገኙም የሕክምና እርዳታ ሊያገኙ አልቻሉም።

በአሁን ሰዓት የጥርስ ሐኪም ሆኖ የይድረሱልኝ የስልክ ጥሪ የማይደርሰው አንድም ሐኪም የለም ይላል የጥርስ ሐኪሞች ማህበር።

ማኅበሩ እንደሚለው አንዳንድ የጥርስ ህመሞች በፍጥነት ሕክምና ካላገኙ ሕይወትን ያህል ክቡር ነገር ሊቀጥፉ የሚችሉበት እድል አለ።

ይህንኑ ስጋቱንም ለእንግሊዝ የብሔራዊ ጤና አገልግሎት አስታውቋል።

ኬቲ ሄይ የ47 ዓመት ሴት ስትሆን በሥራዋ መምህርት ናት።

‹‹ባለፈው ሐሙስ ከፍተኛ የጥርስ ሕመም ቀሰቀሰኝ፤ ለሀኪሜ ስልክ ደወልኩለት፤ ፊትሽ እስካላበጠ ድረስ ላክምሽ አልችልም አለኝ›› ትላለች።

‹‹ወደ 20 ለሚሆኑ የጥርስ ሐኪሞች አድራሻቸውን በኢንተርኔት እየፈለኩ ሁሉ ደውዬላቸዋለሁ። የሁሉም ምላሽ ተመሳሳይ ነው›› ብላለች። መምህርት ኬቲ ዛሬም ድረስ በህመም ማስታገሻ ነው ያለችው።