የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ምንድናቸው? መቼ ነው ሐኪም ቤት መሄድ ያለብኝ?

ማድረግ ያለብን

ለመሆኑ የኮሮናቫይረስ ምልክቶች ምንድናቸው? መቼስ ነው ወደ ሕክምና መሄድ የሚመከረው?

የኮሮናቫይረስ ሁለት ዋነኛ ምልክቶች ከፍተኛ ትኩሳትና ደረቅ ሳል ናቸው። በአንዳንድ ታማሚዎች ላይ እነዚህ ምልክቶች ወደ ትንፋሽ ማጠር ይወስዳሉ። ደረቅ ሳል ሲባል በጣም ጠንካራ የሆነ አንዳንድ ጊዜ ለአንድ ሰዓት የሚቆይ ነው። ከዚህ በፊት ደረቅ ሳል ካለብዎ የኮሮናቫይረስ ሳል በጣም ለየት ያለና ከባድ መሆኑን ማስተዋል ይችላሉ።

ከፍተኛ ትኩሳት የሚባለው ደግሞ የሰውነት ሙቀት መጠን ከ37.8 ዲግሪ ሴልሲየስ ሲልቅ ነው። ይህ ትኩሳት ሰውነት እንዲግል ወይም ደግሞ ከፍተኛ ብርድና መንቀጥቀጥ እንዲሰማን ያደርጋል።

ከእነዚህ ሁለቱ ዋነኛ ስሜቶች ባለፈ ራስ ምታትና ተቅማጥ አንዳንድ የበሽታው ታማሚዎች ያሳይዋቸው ምልክቶች ናቸው። የማሽተትና የመቅመስ አቅም ማጣትም ምልክቶች ሆነው ተመዝግበዋል።

ምልክቶቹ ቫይረስ ሰውነት ውስጥ በገባ በአምስት ቀናት ሊታዩ ይችላሉ። የዓለም ጤና ድርጅት ዘገባ ምልክቶቹ እስከ 14 ቀናት ድረስ ሳይታዩ ሊቆዩ እንደሚችሉ ያስረዳል።

መቼ ነው ወደ ሆስፒታል መሄድ ያለብኝ?

በርካታ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች በቂ እረፍትና እንደ ፓራሲታሞል ያለ ሕመም ማስታገሻዎች ከወሰዱ ያገግማሉ።

ሰዎች ወደ ሕክምና ጣቢያ መሄድ ያለባቸው የአተነፋፈስ ችግር ካጋጠማቸው ነው። ዶክተሮች የታማሚን ሳንባ ከመረመሩ በኋላ አስፈላጊውን ሕክምና ያዛሉ። አስፈላጊ ከሆነ ኦክስጂንና ቬንቲሌሽን ሊታዘዝ ይችላል።

ነገር ግን ሰዎች በሽታው ይዞኛል ብለው ከጠረጠሩ አስቀድመው ወደ ነፃ የእርዳታ መስጫ ቁጥሮች ቢደውሉ ይመከራል። የኢትዮጵያ ነፃ መስመር 8335 ወይም 952 ነው።

የመተንፈስ ችግር ካለብዎ በተለይ ደግሞ ከጥቂት ቃላት ብቻ ማውጣት ካልቻሉ ደውለው ሐኪም ቢያማክሩ ይመረጣል።

የድንገተኛ ክፍል እና የህብረተሰብ ጤና ስፔሻሊስት ዶ/ር ፅዮን ፍሬው የጤና ሚንስትር አማካሪ ናቸው። በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ በሆነባት አሜሪካ፣ ኒውዮርክ የሚገኙት ዶ/ር ፅዮን እንደሚሉት፤ ወደ ህክምና መስጫ ሳይሄዱ ቤታቸው ማገገም የሚችሉ ሰዎች አሉ።

"ሆስፒታል መሄድ የሚያስፈልጋቸው ከ10 በመቶ በታች ናቸው። በእድሜ የገፉ ሰዎችና የተለያየ ህመም ያለባቸው ሰዎች ሆስፒታል መሄድ ይኖርባቸዋል። ነገር ግን ወጣቶችና ሌላ በሽታ የሌለባቸው ሰዎች ቤት እንዲሆኑ ይመከራል" ይላሉ።

በተለይም የህክምና መስጫ ተቋሞች ሁሉንም ሰው ማስተናገድ በማይችሉበት ወቅት ወጣቶችና ሌላ በሽታ የሌለባቸው ሰዎች በቤታቸው እንዲያገግሙ እንደሚደረግ ያስረዳሉ።

አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ባጠቃላይ ሆስፒታል እየገቡ መሆኑን የሚያጣቅሱት ዶ/ር ፅዩን፤ ቁጥሩ እየበዛ ከሄደ ግን ሆስፒታሎች መቋቋም እንደማይችሉ ይናገራሉ።

በአሜሪካ፣ በቻይና እና በአውሮፓ አገራትም አንዳንድ ሰዎች በቤታቸው እንዲያገግሙ የተደረገውም ቁጥሩ በመጨመሩ መሆኑንም ያስረዳሉ። ሆኖም ግን መተንፈስ የሚቸገሩ ሰዎች በሆስፒታል ህክምና እንዲከታተሉ እንደሚደረግም አያይዘው ያነሳሉ።

"ቤታቸው ሆነው እንዲያገግሙ የሚጠበቁ ሰዎች ሌላ ጊዜ ጉንፋን ሲይዛቸው ለራሳቸው የሚያደርጉትን እንክብካቤ እንዲያደርጉ ይመከራል። ትኩሳት እና ሳል የሚያስታግስ ነገር በቤታችን ማድረግ እንችላለን" ይላሉ።

ሆኖም ቤት ውስጥ በእድሜ የገፉ ሰዎች ካሉ፤ በሽታው በነሱ ላይ ሊበረታ ስለሚችል፤ ከነሱ ጋር ንክኪ አለማድረግ ወይም መራቅ እንደሚያስፈልግ ዶክተሯ ይናገራሉ። ቤት ውስጥ ለታመመ ሰው እንክብካቤ የሚያደርጉ ሰዎች በበሽታው እንዳይያዙ፤ ታማሚው/ዋ በአግባቡ እጅ መታጠብ ይጠበቅበታል (ይጠበቅባታል)። በተጨማሪም ህሙማን ለብቻቸው በአንድ ክፍል እንዲቆዩ ከሰዎች በሁለት ሜትር እንዲርቁም ይመክራሉ።

ፅኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ምን አለ?

አይሲዩ የሚል ሙያዊ ስያሜ የተሰጠው የፅኑ ሕሙማን ክፍል በጣም ለታመሙ ሰዎች የተዘጋጀ ሥፍራ ነው።

እዚህ ክፍል የሚገቡ ሰዎች ለመተንፈስ እንዲረዳቸው ኦክሲጅን ይሰጣቸዋል። ቬንቲሌሽን የተሰኘው ቁስ የሚገጠመው በጣም ለታመሙ ሰዎች ብቻ ነው። መሣሪያው በርከት ያለ ኦክሲጅን ለታማሚው ያቀርባል።

መከከለኛ ምልክት ከታየብኝ ምን ላድርግ?

መካከለኛ የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች ቢያንስ ለአንድ ሳምንት ቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩ ይመከራሉ። በርካታ ሃገራት መለስ ያለ ምልክት ያሳዩ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያገሉ ነው የሚያደርጉት እንጂ የሚሰጣቸው ለየት ያለ ሕክምና የለም።

የዓለም ጤና ድርጅትም ቢሆን ሰዎች ራሳቸውን እንዲያገሉ ነው የሚመክረው።

ሰዎች ቴርሞሜትር የተሰኘውን መሣሪያ በመጠቀም የሙቀት ልኬታቸውን ማወቅ ይችላሉ። የሰውነት ሙቀታቸው ከ37.8 በላይ የሆኑ ሰዎች ሕክምና እንዲያገኙ ይመከራሉ።

ኮሮናቫይረስ ምን ያህል ገዳይ ነው?

ምንም እንኳ ይህ መረጃ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ባይሆንም ከኮሮናቫይረስ የመሞት ዕድል በጣም ዝቅ ያለ ነው [በመቶኛ ሲሰላ ከ2 በመቶ አይበልጥም]።

የቫይረሱን ገዳይነት ዝቅ ያደረገው ምናልባትም ብዙ ታማሚዎች ባለመርመራቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል።

የዓለም ጤና ድርጅት 56 ሺህ ሰዎች ላይ ምርመራ አካሂዶ፡

  • 6 በመቶ በጣም የታመሙ ሆነው ተገኝተዋል - ከሳንባ አለመሥራት እስከ ለሞት መጋለጥ
  • 14 በመቶ ጠንከር ያለ ምልክት ታይቶባቸዋል - የመተንፈስ ችግርና ትንፋሽ ማጠር
  • 80 በመቶ ደግሞ መካከለኛ የሚባል ምልክት አሳይተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በርካታ ሰዎች ባይመረመሩም በቫይረሱ ተይዘዋል ይላል።