ቻይና ዉሃንን ከፍታ ስዊፌ ከተማን ለምን ዘጋች?

ቻይና

የፎቶው ባለመብት, AFP/ GETTy

ቻይና የኮቪድ-19 መነሻ ናት የምትባለውን የ11 ሚሊዮን ሕዝቦች መኖርያ ውሃንን ትናንት ሙሉ በሙሉ ክፍት አድርጋለች፡፡ 7ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ከውሃን ከተማ ወጥተዋል ተብሏል፤ የትናንቱን ውሳኔ ተከትሎ፡፡

በምትኩ ግን አንዲት ከተማ ተቆልፋለች፡፡ ስዊፌ ትባላለች፡፡ 100ሺ ሰዎች የሚኖሩባት ትንሽዬ የድንበር ከተማ ነች፡፡ ከራሺያ የምትዋሰን ሩቅ ከተማ ናት፡፡ ከቤጂንግ 1ሺ ማይል ትርቃለች፡፡

በዚች ከተማ ነዋሪዎች በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ከቤት እንዳይወጡ ተነግሯቸዋል፡፡

600 አልጋ ያለው ሆስፒታልም እየተገነባላቸው ነው፡፡ ሆስፒታሉ ሰኞ ተጀምሮ እሑድ ይመረቃል፡፡

አንድ የአከባቢው ነጋዴ ለቢቢሲ ‹‹በጣም ፈርቻለሁ›› ሲል ተናግሯል፡፡ ሌላ ነዋሪ ደግሞ በመንግሥቴ እተማመናለሁ ይላል፡፡

ረቡእ እለት ቻይና 59 ሰዎች በኮሮና መያዛቸውና እነዚህ በሙሉ ከውጭ የመጡ መሆናቸውን አሳውቃ ነበር፡፡

የአገሬው ሚዲያዎች ይፋ እንዳደረጉት ከሆነ ከነዚህ ከውጭ ገቡ ከተባሉት ውስጥ 25ቱ ከዚች ስዊፌ ከተባለች ድንበር ከተማ የመጡ ነበሩ፡፡

አብዛኛዎቹ ታማሚዎች ከሞስኮ ወደ ቪላቮስኮት የተጓዙና ከዚያም በዚች ከተማ አድርገው ወደ ቻይና የገቡ ናቸው፡፡

ሌሎች ከዚህ ከተማ ወደ መሀል ቻይና የገቡ 86 ሰዎች የኮቪድ-19 ምልክት የማያሳዩ፤ ነገር ግን ቫይረሱ ያለባቸው ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የቻይና መንግሥት ዕቃ የጫኑ ካርጎዎች ካልሆኑ በዚያ ድንበር በኩል መንገደኛ እንዳይተላለፍ መመሪያ አስተላልፏል፡፡

የድንበር ከተማዋ ነዋሪዎች ቤት እንዲቀመጡ የተነገራቸው ሲሆን ከየቤቱ አንድ ሰው በ3 ቀን አንድ ጊዜ አስቤዛ ለማድረግ ከቤት መውጣት ይቻላል፡፡

አዲስ የሚሰራው ሆስፒታል ታዲያ በመጪው እሁድ በሩን ለታማሚዎች ክፍት ያደርጋል ተብሏል፡፡

ቻይና የወረርሽኙ መነሻ ብትሆንም የደረሰባት ሰብአዊ ጉዳት ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸር የከፋ አይደለም፡፡

በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙም ሆነ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ይገኛል፡፡ ባለፈው ማክሰኞ እንዲያውም አንድም ታማሚ ያልተመዘገበበት እለት ሆኖ ውሏል፡፡

ሁኔታዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ ለ11 ሳምንታት ተዘጋግታ የነበረችው ውሃን ከተማ የተከፈተችው በትናንትናው እለት ረቡእ ነበር፡፡

ይህ ከመሆኑ ታዲያ 221 ገቢና ወጪ በረራዎች በአንድ ቀን ተደርገዋል፡፡ 7ሺ ሰዎች ዉሃንን ለቀዋል፡፡ 4ሺ 500 ሰዎች ደግሞ ገብተዋል፡፡

ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ የተለያዩ የሕዝብ ማመላለሻዎችን ተጠቅመዋል፡፡

ቤጂንግ አሁንም ከውሃንም ሆነ ከሌላ ቦታ የሚመጡ ቻይናዊያንን ሳትመረምር አታስገባም፡፡

ደህና ቢሆኑ እንኳ ከውሃን የመጡት ለ14 ቀናት ተገለው ይቀመጣሉ፤ ክትትልም ይደረግባቸዋል፡፡