ኮሮናቫይረስ ለምን ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ ወንዶችን ያጠቃል?

የወንድ ስዕል

በርካቶች የኮሮናቫይረስ ምልክት ታይቶባቸው፣ ሐኪም ቤት መሄድ ሳይጠበቅባቸው በሳምንታት ውስጥ ሊያገግሙ ይችላሉ። ነገር ግን ለማገገም የግድ ሕክምና ማግኘት የሚያስፈልጋቸውም አሉ።

እድሜያቸው ከ70 የዘለለ እና ህመም ያለባቸው ሰዎች ለበሽታው የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።

ኮሮናቫይረስ እድሜያቸው በ50ዎቹና በ60ዎቹ ክልል ያሉ ወንዶችን በብዛት ሲያጠቃ ተስተውሏል። በሽታው እነሱን ብቻ ያጠቃል ማለት ባይሆንም እስካሁን ጎልቶ የታየው በዚህ እድሜ ክልል ላይ ነው።

በእድሜ የገፉ ወንዶች ለምን በቫረይሱ ይጠቃሉ?

ተመራማሪዎች ለዚህ ጥያቄ እርግጠኛ መልስ የላቸውም።

ከዩናይትድ ኪንግደም የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው፤ በፅኑ የታመሙ ሰዎች አማካይ እድሜ 60 ነው። አብዛኞቹ ደግሞ ወንዶች ሲሆኑ፤ እንደ ልብ ህመም ያለ በሽታ ያለባቸውና ከመጠን ያለፈ ውፍረት የገጠማቸው ናቸው።

በዚያው አገር ከሞቱት 647 ሰዎች 44ቱ ከ45 ዓመት እስከ 65 ናቸው። ይህም ካጠቃላይ ቁጥሩ 7 በመቶ ነው።

ሴቶችም ይሁን ወንድ አዛውንቶች የመሞት እድላቸው ከወጣቶች ቢበልጥም፤ የወንድ አዛውንቶች የመሞት እድል በየትኛውም እድሜ ካሉ ሴቶች ይልቃል።

ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ቻይና፣ ዉሃን የተገኘው መረጃም የሚያሳየውም ይህንኑ ነው።

ሆኖም ግን ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ ለቫይረሱ ተጋላጭነትን ከፆታ ጋር ብቻ ማስተሳሰር አይቻልም። ሲጋራ ማጤስ እና ሌሎችም ተጋላጭ ሊያደርጉ ይችላሉ።

የኖቲንግሀም ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ኢን ሆል፤ "ወንዶችን ተጋላጭ የሚያደርጋቸው ይህ ብቻ ነው ብዬ አላምንም፤ ገና ያልደረስንበት ነገር አለ" ይላሉ።

ወንዶች ከሴቶች በበለጠ በልብ ህመም፣ በስኳር እና በሳምባ በሽታ ይያዛሉ።

አንዳንድ ተመራማሪዎች ዘረ መል እና ሆርሞን ከበሽታው ተጋላጭነት ጋር ግንኙነት አላቸው ብለው ይገምታሉ።

ሴቶች በሽታውን የመከላከል አቅም አላቸው?

የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር ፊሊፕ ጎልደር የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅም (ኢምዩኒቲ) አጥኚ ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት፤ በሴቶች እና በወንዶች መካከል በሽታን የመከላከል አቅም ልዩነት አለ። ይህ ልዩነት ጎልቶ የሚስተዋለው ደግሞ በተላላፊ በሽታዎች ላይ ነው።

ሴቶች በሽታ የመከላከል አቅማቸው የበለጠ የሆነው ሁለት ኤክስ ክሮሞዞም (X chromosome) ስላላቸው እንደሆነ አጥኚው ያስረዳሉ። በእነዚህ ላይ በሽታን የሚከላከሉ ዘረ መሎች እንደሚገኙም ያስረዳሉ።

በዩናይትድ ኪንግደም በየዓመቱ 600 ሺህ ሰዎች ይሞታሉ። ብዙዎቹ አዛውንቶችና የተለያየ ህመም ያለባቸው ናቸው። ከኮሮናቫይረስ ጋር ከተያያዙ ህልፈቶች ጋርም የተስተዋለው ተመሳሳይ ነገር ነው።

ራስን ከበሽታው ለመከላከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር እና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ይመከራል። ሲጋራ ማጨስ ማቆምም ያስፈልጋል።

ወንዶች ከሴቶች በበለጠ ሲጋራ ያጨሳሉ፣ ጨው የበዛበት ምግብ ይበላሉ፣ ቀይ ሥጋን ይመገባሉ፣ መጠጥ ይጠጣሉ፣ አትክልትና ፍራፍሬም አይመገቡም ተብሏል።