ነዳጅ አምራች አገራት በታሪክ ከፍተኛ የተባለለት ስምምነት ላይ ደረሱ

ይህ ስምምነት በታሪክ ትልቁ የተባለለት ነው

የፎቶው ባለመብት, TASS / GETTY IMAGES

በኮሮናቫይረስ ምክንያት የፍላጎት መቀዛቀዝ የታየበትን የነዳጅ ምርት እንዲያንሰራራ ለማድረግ ሲባል የነዳጅ አምራች አገራት ኅብረት ኦፔክና አጋሮቹ ታሪካዊ የተባለ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ስምምነቱ በዋናነት የዓለም የነዳጅ ምርትን በ10 እጅ መቀነስ ላይ ያተኮረ ነው።

ትናንት እሑድ በቪዲዮ ስብሰባ የተቀመጡት የነዳጅ አምራች አገራት ኅብረትና አጋሮቻቸው የደረሱበት ይህ ስምምነት በታሪካቸው ትልቁ ነዳጅ ምርትን ለመቀነስ ያደረጉት ስምምነት ተብሏል።

አገራቱ ስምምነት ላይ ደርሰው የነበረው ቀደም ብሎ ቢሆንም ሜክሲኮ ግን ስምምነቱን ሳትደግፍ ቆይታለች። አሜሪካ ሜክሲኮ እንድትቀንስ የሚጠበቅባትን ያህል የነዳጅ ምርት በሜክሲኮ ፈንታ ለመቀነስ ቃል በመግባቷ ስምምነቱ ሊፈረም ችሏል።

ስምምነቱ ተግባራዊ ሲሆን ወደ 10 ሚሊዮን በርሜል የነዳጅ ምርት በየቀኑ ሳይመረት ይቀራል ማለት ነው።

ይህ ስምምነት ታሪካዊ የሚያስብለው ከፍተኛ ምርትን ለመቀነስ በመወሰኑ ብቻ ሳይሆን በስምምነቱ የተካተቱ አገራት ብዛት ጭምር ነው። የኦፔክ አገራትና አጋሮቻቸውን ጨምሮ ሌሎች እንደ ኖርዌይ፣ አሜሪካ፣ ብራዚልና ካናዳ ጭምር የሚፈርሙት መሆኑ ነው።

ምርት የመቀነስ ስምምነቱ ሊዘገይ የቻለው ሳኡዲ አረቢያና ሩሲያ እልህ ተጋብተው ስለነበረ ነው ተብሏል።

በስምምነቱ መሰረት ከግንቦት 1 ጀምሮ አገራቱ ምርታቸውን በ10 እጅ ይቀንሳሉ። ይህም ማለት በቀን 10 ሚሊዮን በርሜል ነው፤ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ኖርዌይና ብራዚል ሌላ 5 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ከዕለታዊ ምርታቸው ይቀንሳሉ።

ከሐሌ ጀምሮ ግን ምርት እየጨመሩ ሄደው ምርት ቅነሳው በቀን ከ10 ሚሊዮን በርሜል ወደ 8 ሚሊዮን በርሜል እየወረደ ይመጣል።

ከወር በፊት የነዳጅ ዋጋ በ18 ዓመት ታሪክ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁሎ ነበር።