ኮሮናቫይረስ፡ በድብቅ በተዘጋጀ ድግስ ላይ በተፈጸመ ጥቃት 6 ሰዎች ቆሰሉ

ፖሊስ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመቆጣጠር ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ባዘዘችው የአሜሪካዋ ግዛት ካሊፎርኒያ ውስጥ በድብቅ በተዘጋጀ ድግስ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ስደስት ሰዎች በጥይት መቁሰላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

ተኩሱ የተከሰተው ባለፈው አርብ ሌሊት ላይ ቤከረስፊልድ ተብሎ በሚታወቅ የመኖሪያ ህንጻዎች ጊቢ ውስጥ እንደሆነ የአካባቢው ፖሊስ ገልጿል።

በጥቃቱ የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው አራት ሴቶች፣ አንድ ወንድና አንዲት ታዳጊ ሲሆኑ፤ የህክምና እርዳታ ማግኘታቸውና ጉዳቱም ህይወታቸውን ለክፉ የሚሰጥ እንዳልሆነ ተነግሯል።

ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለ ሰው ባይኖርም፤ በመኪና ከአካባቢው ሲሸሹ የታዩ አራት ሰዎች ጥቃቱን ፈጽመዋል ተብለው ተጠርጥረዋል።

ፖሊስ እንዳለው በተፈጸመው ጥቃት ላይ ምርመራ እየተካሄደ ነው።

በካሊፎርኒያ ግዛት ውስጥ ሁሉን አቀፍ የእንቅስቃሴ ዕገዳ ከባለፈው መጋቢት ወር አንስቶ ተግባራዊ ሆኖ ይገኛል።

ግዛቲቱ በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተመቱት የአሜሪካ ግዛቶች አንዷ ስትሆን አስካሁንም ከ21 ሺህ 800 በላይ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን 651 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።

በዚህም ሳቢያ የካሊፎርኒያ ግዛት አስተዳዳሪ ጋቪን ኒውሰም ባወጡት ትዕዛዝ ነዋሪዎች ምግብና መድኃኒት እንዲሁም ስፖርት ለመስራት ካልሆነ በስተቀር ከቤታቸው እንዳይወጡ ተከልክለዋል።

በግዛቲቱ ውስጥ የሚገኙ አስፈላጊ ያለሆኑ መደብሮች እንዲዘጉ የተገደዱ ሲሆን የምግብ መደብሮች፣ መድኃኒት ቤቶችና የነዳጅ ማደያዎች ብቻ ክፍት እንዲሆኑ ተደርጓል።