ኮሮናቫይረስ፡ ቢሊየነሩ ቢልጌትስ የኮሮናቫይረስ ሊከሰት እንደሚችል እንዴት ቀድመው ሊያውቁ ቻሉ?

ቢል ጌትስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአማዞኑ ጄፍ ቤዞስ በሀብት ዓለምን ይመራል። 56 ዓመቱ ነው። አግብቶ ፈቷል። አራት ልጆች አሉት። ሀብቱ 124.7 ቢሊዮን ዶላር አልፏል።

ቢል ጌትስ ይከተላሉ። ዕድሜያቸው 64 ነው። ከባለቤታቸው ሜሊንዳ ሦስት ልጆችን አፍርተዋል። 104.1 ቢሊዮን ዶላር ሀብት አላቸው።

ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ግን የየትኛውም ቢሊየነር ስም እንደ ቢልጌትስ ተደጋግሞ አይነሳም። ለምን?

እርግጥ ነው ከ2 ወራት በፊት በቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በኩል 100 ሚሊዮን ዶላር ለኮሮናቫይረስ ሕክምናና ተያያዥ ጉዳዮች ወጪ እንደሚያደርጉ ይፋ አድርገዋል። ሆኖም በዚህ በጎ ተግባራቸው አይደለም ይበልጥ ስማቸው እየተነሳ ያለው።

ምክንያቱም ቢል ጌትስ ወትሮም መስጠት ብርቃቸው አይደለም። እንዲያውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማይክሮሶፍት ኩባንያ ያላቸው ድርሻ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። አብዛኛውን ድርሻቸው ሽጠውታል፤ ወይም አሳልፈው ሰጥተዋል። አሁን በእጃቸው የቀረው ከጠቅላላው 2 እጅ እንኳ አይሞላም።

ሀርቫርድን ጥለው ወጥተው ከአጋራቸው ፖል አለን ጋር የመሠረቱት ማይክሮሶፍት ኩባንያ የቦርድ አባልም ነበሩ፤ ለረዥም ዘመን። እሱንም ኃላፊነታቸው ከሳምንት በፊት በፈቃዳቸው ለቅቀዋል።

ጌትስ እጅግ ለጋስ ከመሆናቸው የተነሳ እስከዛሬ 36.8 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የማይክሮሶፍ ኩባንያን ስቶክ በእርዳታ መልክ ሰጥተዋል።

ታዲያ ሰውዬውን ከኮሮናቫይረስ ጋር የሚያገናኛቸው ምንድነው?

የሴራ ፖለቲካ አራማጆች ኮሮናቫይረስ በአንዳች አሻጥር የተፈጠረ የቤተ ሙከራ ውጤት እንጂ ከቻይና ሁቤይ ግዛት፣ ከዉሃን ከተማ የእንሰሳት ሥጋ ተዋጽኦ ጉሊት የተነሳ አይደለም ይላሉ።

ሴራቸውን ፈትለው ሲጠልፉትም እንዲያውም ቢልጌትስ በቤተ ሙከራ ራሱ የፈጠረው ቫይረስ ነው ይላሉ። ለምን ሲባሉ መድኃኒቱን ራሱ አምርቶ ለመቸብቸብ ሲሉ ይመልሳሉ ከፊሎቹ፤ ሌሎች ደግሞ የዓለምን ሕዝብ ለመቀነስ ሊሆን ይችላል ይላሉ።

የዴይሊ ሾው አሰናጅ ትሬቨር ኖዋ በቅርቡ ለቢልጌት ባደረገው ቃለ ምልልስ የመጀመርያ ጥያቄ ያደረገውም ይህንኑ የሴራ ሸራቢዎችን ጥርጣሬ ነው።

"ቢል፣ ኮሮናን 'ብዬ ነበር' ለማለት ራስህ የፈጠርከው ቫይረስ ነው ይባላል፤ ለመሆኑ ከ5 ዓመት በፊት የተነበይከው በትክክል ስለዚህ ቫይረስ ነበር ወይስ ስለሌላ ተመሳሳይ ቫይረስ?" ሲል ጠይቆታል።

ቢል ጌትስ ሲመልሱም "እኔ ኮሮናቫይረስ ዛሬ ልክ አሁን በተፈጠረበት ጊዜ ይፈጠራል ብዬ አልተነበይኩም፤ ይህ እንደሚሆንም አላውቅም ነበር። ያን ትንቢት የተናገርኩት መንግሥታት ለማይቀረው ወረርሽኝ በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ ለማበረታታት ነበር፤ በሚያሳዝን ሁኔታ ያ ሳይሆን ቀርቶ የፈራሁት ደረሰ" ብለዋል።

ኮማኪው ትሪቨር ኖዋ ሌላ ጥያቄን አስከተለ፡

"አንተ አንድ ግለሰብ ነህ? እንዴት ነው መንግሥታት እንኳ ሊያውቁ ያልቻሉትን ልታውቅ የቻልከው?"

ቢል ጌትስ ሲመልሱ፣ "እኔ ብቻ አይደለሁም ስጋቴን ቀድሜ የገለጽኩት፤ እኔ በፈራሁት ያህል ይህ እንዳይደርስ ስጋታቸውን ሲያሰሙ የነበሩ ብዙ ሳይንቲስቶች ነበሩ፤ አንዱ ዶ/ር ፋውቺ ነው" ብለዋል።

ጨምረውም፤ "ኢቦላ፣ ዚካ፣ ሳርስና መርስ መጥተው ሄደዋል፤ እድለኞች ነን እልቂት ባለማድረሳቸው። በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ የሚችል ወረርሽኝ ወደፊት ቢከሰት ሊያስከትል የሚችለውን ነገር ሳስብ እንቅልፍ ይነሳኝ ነበር፤ ያንን ጭንቀቴን ነው የተናገርኩት. . . " ብለዋል ቢልጌትስ።

የሴራ ፖለቲካ በመረጃ ላይ የማይመሰረት የቢሆን ዓለም በመሆኑ የቢል ጌትስ ምላሽ ለብዙዎች የሚታመን ላይሆን ይችላል።

ሴራ አራማጆች ቁልፍ ጉዳይ አንስተው ያሻቸውን ሰውና ክስተት አንዱን ካንዱ ይሸርባሉ። ከዚያ ስሜት እንዲሰጥ ከስጋት ጋር ያስተሳስሩታል።

ቢል ጌትስ ይህ እንደሚመጣ ቀድመው ማወቃቸው የሴራ ፖለቲካ አራማጆች ሁነኛ አጀንዳ ከሆኑ ሰነባብተዋል። "ቢሊየነሮች ድሃውን የዓለምን ሕዝብ ለመቀነስ" ስለማሴራቸው የቢልጌትስን ንግግር እንደ አንድ ማስረጃ የሚያቀርቡትም ለዚሁ ነው።

"ኮምፒውተር ይፈጥራሉ፤ ከዚያ መተግበሪያውን፣ ከዚያ ቫይረሱን፤ አሁን ደግሞ ይህን ወደ ሰው በማምጣት ወረርሽኝ ፈጥረው፣ ከዚያ ክትባቱን፣ ከዚያ መድኃኒቱን እያሉ በዓለም ሕዝብ ይጫወታሉ" ይላል የሴራ ትንተና አራማጆች ክስ።

ቢል ጌትስ በ"ቴድቶክ" ምን ነበር የተነበዩት?

ቴድቶክ ተጽእኖ ፈጣሪዎች በሰዓት የተገደበ ንግግር የሚያደርጉበት ዓለም አቀፍ መድረክ ነው። ቢል ጌትስ ከአምስት ዓመት በፊት ያደረጉትን ይህን ንግግር ከ25 ሚሊዮን ሰዎች በላይ በዩቲዩብ መስኮት ተመልክተውታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ቢል ከባለቤታቸው ሜሌንዳ ጌትስ ጋር

እርግጥ ነው ይህ በፈረንጆች ማርች፤ 2015 በካናዳ ቫንኩቨር ቢል ጌትስ ያደረጉት ንግግር "እኚህ ሰው ነብይ ነበሩ እንዴ?" የሚያስብል ነው፤ ያለማጋነን።

ያኔ ማንም ልብ ያላለው ይህ አስገራሚ ንግግራቸው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ሚሊዮኖች በድጋሚ እየተመለከቱት ነው።

የዚህ ንግግራቸው ጭብጥ በመጪው ጊዜ የዓለም ስጋት ኒውክሌር ቦምብ ሳይሆን ቫይረስ ነው የሚል ነው። በቅርብ ዓመት አንዳች የቫይረስ ወረርሽኝ መጥቶ ሺዎችን እንደሚገድልም ይተነብያሉ። ይህን ለማስረዳትም አንድ በርሜል እያንከባለሉ ነበር ወደ መድረኩ የወጡት።

"ልጅ ሳለሁ ዋንኛው ስጋት የኑክሌር ጦርነት ነበር፤ በቤታችን ጓሮ ምድር ቤት ውስጥ ውሃና ምግብ ማጠራቀሚያ እንዲሆነን ይህንን በርሜል እናስቀምጥ ነበር" ሲሉ ንግግራቸው ጀምራሉ።

አሁን ግን ኒውክሌር ሳይሆን ቫይረስ ነው የዓለም ስጋት ሲሉ ትንቢታቸውን ይቀጥላሉ።

"ለዚያ አይቀሬ የቫይረስ ወረርሽኝ አሁን ዝግጅት ካልጀመርን ኋላ ጉድ ነው የሚፈላው" ሲሉም ንግግራቸውን ይቋጫሉ። እንዴት ታያቸው?

ትናንት ምሽት ደግሞ ከቢቢሲ ብሬክፋስት የቴሌቪዥን መሰናዶ ጋር ቆይታ አድርገው ነበር ቢል ጌትስ። በዚህ ቆይታቸው ያሰመሩበት ነጥብ "ዓለም ለዚህ ወረርሽኝ ቀደም ብሎ ተዘጋጅቶ ቢሆን ኖሮ፣ እንዲሁም ሳይንቲስቶች የሚሉትን ነገር ቀደም ብሎ ሰምቶ ቢሆን ኖሮ. . . ይህ ሁሉ ጥፋት ባልደረሰ ነበር።"

አሁን ባለው ርብርብም ቢሆን ጥቂት አገራት ናቸው አስር ከአስር የሚያገኙት፤ አብዛኛው አገር ለወረርሽኙ የሰጠው ምላሽ በጣም ደካማ ነው ሲሉ ተችተዋል።

"የዓለም መንግሥታት በቅንጅት መሥራት ነበረባቸው" ሲሉ በተጨባጭ ምን ማድረግ ነበረባቸው? ተብለው የተጠየቁት ቢል ጌትስ ወረርሽኙ እስካሁን ሁለት ምዕራፎች እንደነበሩት በማብራራት ጀምረዋል።

የመጀመርያው ቫይረሱ ከቻይና ሳይወጣ የነበረው ጊዜ ሲሆን ሁለተኛው አብዛኛዎቹን ሀብታም አገራትን ካጠቃ በኋላ ያለው ጊዜ ሲሉ ከፍለውታል።

የሀብታም አገራቱ ሁኔታ በመጪው የፈረንጆች በጋ መጀመርያ አካባቢ እየተሻሻለ እንደሚመጣም ተንብየዋል።

"አስፈሪው የወርርሽኙ ምዕራፍ የሚሆነው በታዳጊ አገራት በሽታው የተቀሰቀሰ ዕለት ነው" የሚሉት ቢል ጌትስ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያን ጊዜ የሰበሰበውን ቬንትሌተርም ሆነ ሌሎች የሕክምና መሣሪያዎች በእርዳታ ወደ ታዳጊ አገራት ካላስተላለፈ አስፈሪ ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል። ቻይና ገና ከአሁኑ ያን እያደረገች እንደሆነ በመጥቀስ እውቅና ሰጥተዋት አልፈዋል።

ቢል ጌትስ ስለታዳጊ አገራት ስጋት ገብቷቸዋል

ከቢቢሲ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ቢል ጌትስ ታዳጊ አገራት ይህን ወረርሽኝ ለመቋቋም አንዳችም አቅም እንደሌላቸው አረጋግጠዋል።

በሽታውን ታዳጊ አገራት እንዲቋቋሙት በሀብታም አገራት ካልታገዙ በድጋሚ ወረርሽኙ ወደ ሀብታም አገራት ተመልሶ ሊመጣ እንደሚችልም ስጋታቸውን አጋርተዋል።

ክትባት በትክክል መቼ ሊደርስ ይችላል? ሲል የቢቢሲ ብሬክፋስት አሰናጅ ጋዜጠኛ ሲጠይቃቸው፤ ቢል ጌትስ ቢያንስ 10 ኩባንያዎች እጅግ ተስፋ ሰጪ ምርምር እያደረጉ እንደሆነ ጠቅሰው ክትባቱን ተግባራዊ ለማድረግ በትንሹ 18 ወራት እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል።

ይህም የሚሆነው መንግሥታትና የመድኃኒት ቁጥጥር ኤጄንሲዎች ወትሮ ለመድኃኒት ሙከራ አስገዳጅ ሂደት የነበሩ ነገሮችን ካለው አጣዳፊ ሁኔታ በመነሳት ማንሳት ሲችሉ እንደሆነም ተናግረዋል።

"ለምሳሌ በተለመደው አሰራር አንድ አዲስ መድኃኒት ከተወሰደ ከ2 ዓመት በኋላ ምን የጎንዮሽ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል የሚለው ነገር የመድኃኒት ምርት በገፍ መመረት ከመጀመሩ በፊት መጠናት አለበት። ይህ ግን አሁን ካለው ጥድፊያ አንጻር በኮሮናቫይረስ ክትባት ሂደት ሊተገበር የሚችል አይደለም" ብለዋል ቢል ጌትስ።

ብዙ ጥብቅ የነበሩ የመድኃኒት ምርት ሂደቶች ደረጃዎች ሕይወትን ለመታደግ ሲባል ሊታፈሉ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

ከአምስት ዓመት በፊት በቴድቶክ መድረክ ያደረጉት ንግግር አሁን ስለተከሰተው ወረርሽኝ የሚተነብይ እንደነበር ያስታወሰው የቢቢሲ ጋዜጠኛ "ያን ጊዜ ምነው የዓለም መንግሥታት ሰምተውኝ ቢሆን ኖሮ" የሚል ስሜት ተፈጥሮባቸው እንደሆነ ጠይቋቸው ነበር።

ቢል ጌትስ ሲመልሱ መንግሥታት ጦርነት ቢከሰት ብለው በጋራም ሆነ በተናጥል የጦር ልምምድ እንደሚያደርጉ አስታውሰው፣ ጦር ሜዳ ከሚያልቀው ሕዝብ በላይ ለሚጨርስ የተህዋሲያን ወረርሽኝ ግን ምንም ግድ አልነበራቸውም፣ በጀትም አይመድቡም ነበር ብለዋል።

ኮሮናቫይረስ ካለፈ በኋላ ዓለም የሚቀጥለውን ወረርሽኝ እንደከዚህ በፊቱ እጁን አጣጥፎ ተቀምጦ ይጠብቅ ይመስልዎታል ወይ? ተብለው የተጠየቁት ቢል ጌትስ "ይህ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።

ኮማኪው ትሬቨር ኖዋ ቢል ጌትስን እንግዳ ባደረገበት መሰናዶው ለቢል ጌት በመጨረሻ ካቀረበላቸው ጥያቄዎች መሀል አንዱ የሚከተለው ነበር፡-

"ይህ እንደሚመጣ ተንብየው ሆኖልዎታል? ቀጥሎ የሚመጣብንን መቅሰፍት ሊነግሩን ይችላሉ? ከአሁኑ እንድንዘጋጅ?"

ቢል ጌትስ ጥያቄውን በፈገግታ ነበር የመለሱለት። ዓለም ከኮረናቫይረስ ቅጣት በቂ ትምህርት መውሰዱን ያመኑ ይመስላሉ።