ኮሮናቫይረስ፡ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በየመን የሚገኙ ኢትዯጵያውያን ስደተኞች ለኮሮናቫይረስ እንዳይጋለጡ ስጋት አለኝ አለ

በድንበር ላይ ያሉ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, SM

ዓለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት በሳኡዲ አረቢያና የመን ድንበር በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለኮሮናቫይረስ ለአደጋ ተጋልጠዋል ሲል አስታወቀ።

ቢቢሲ ባለፈው ሳምንት ያናገራቸውና በየመንና ሳኡዲ ድንበር አቅራቢያ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ባገኘው መረጃ መሰረት ከሁውቲ ታጣቂዎች በደረሰባቸው ጥቃት በየበረሃው መበተናቸውን ገልፀው ነበር።

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ሄዶን ኦሊቪያ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ድርጅታቸው ስለሁኔታው እንደሚያውቅ አረጋግጠው ይህም እንደሚያሳስበው እና ስጋት እንደገባው ገልፀዋል።

ድርጅቱ በየበረሃው ተበትነዋል የተባሉት ስደተኞቹን ቁጥር በውል ባያረጋግጥም ምንጮቻችን ግን በግምት ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ ስደተኞች ሰአዳ በተባለ የየመን ግዛት ወደ ሳኡዲ አረቢያ ለመሻገር ሲሞክሩ ከኮሮናቫይረስ ጥርጣሬ ጋር በተያያዘ በሁለቱም ወገኖች መካከል አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል ብለዋል።

እንደ ኃላፊዋ ገለፃ ይህ ስፍራ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ያለበት ቦታ ነው።

ስደተኞቹ ያሉበት ሁኔታን ለቢቢሲ ሲናገሩም በሁውቲ አማፂያንና በመን መንግሥት ወታደሮች መካከል ውጊያ በሚካሄድበት ስፍራ በየዕለቱ ውጊያ እንደሚካሄድ ጠቅሰው "በየዕለቱም ጥይት በላያችን ላይ እያፏጨ በስጋት ነው" ሲሉ ገልፀዋል።

ቢቢሲ በየመን ድንበር አቅራቢያ የሚገኙና አደጋ ላይ ናቸው የተባሉትን ስደተኞች አግኝቶ ለማናገር በስፍራው ስልክ ግንኙነት የተቋረጠ በመሆኑ አልተቻለም።

ቀደም ሲል ከሳምንት በፊት ከ4 ሺህ በላይ ስደተኞች ከመካከላቸው ወደ ሳኡዲ አረቢያ የተሻገሩ መሆኑን የገለፁ ስደተኞች እነርሱም ግን በእስር ቤት እንደሚገኙ ተናግረዋል።

እነዚህ ስደተኞች ስጋት ውስጥ የወደቁት በጦርነቱ ብቻ ሳይሆን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ታዛምታላችሁ በሚል በሚደርስባቸው ጥቃት ጭምር እንደሆነ ይናገራሉ።

ኃላፊዋም በየመን አማፂያንና በሳኡዲ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም አሁን ያለው ስጋት የጦርነት ብቻ ሳይሆን የቫይረሱ መስፋፋት በመሆኑ የስደተኞቹን ስጋት አይቀንሰውም ሲሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ሄዶን ኦሊቪያ አክለውም ድርጅቱ ምን ማድረግ እንዳለበት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ መሆኑንና ያለውን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ሊያሳይ በሚችል መልኩ ጥናት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

አክለውም በስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እንዲቆም እንዲሁም ከኮሮናቫይረስ ጋር በተየያዘ አገራት በበሸታው መከላከል ላይ ስደተኞችን የሚያካትት ስልት እንዲከተሉ እንዲሁም ዜግነታቸውንና ህጋዊነታቸውን ሳይመለከቱ ከዜጎቻቸው ጋር እኩል የጤና አገልግሎት እንዲያቀርቡላቸው ጠይቀዋል።

በዚህ መካከል በጥቃቱ የተወሰኑ ስደተኞች ሞተው ሊሆን ይችላል ሲሉ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ስጋታቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በየመን የኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው መገኘቱ የተገለጸው በሳምንቱ መጨረሻ ነበር።