የኢትዮጵያ አየር ኃይል የአልሻባብ የፈንጂ ቡድን አባላትን ደመሰስኩ አለ

አየር ኃይል

የፎቶው ባለመብት, Tech. Sgt. Cecilio M. Ricardo Jr

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሶማሊያ ውስጥ በአልሻባብ ቡድን አባላት ላይ በወሰደው እርምጃ በርካቶችን መግደሉን የመከላከያ ሠራዊት አስታወቀ።

አየር ኃይሉ ርምጃውን የወሰደው በሶማልያ ልዩ ስሙ ኮርቶሌ እና ህርኩት በተባሉ አካባቢዎች ሲሆን ጥቃቱም የአልሻባብ "17 የፈንጂ ቡድኑ አባላትን ሙሉ በሙሉ መደምሰሳቸውን" የምሥራቅ አየር ምድብ ምክትል አዛዥ ኮሎኔል ሀብቶም ዘነበ ገልጸዋል።

መከላከያ ሠራዊቱ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የአልሻባብ የፈንጂ ቡድን፤ ከዶሎ በመነሳት ወደ ደቡብ ምዕራብ ሶማልያ ባይደዋ የተለያዩ ወታደራዊ ቁሣቁሶችን ጭኖ እየተንቀሳቀሰ በነበረው የኢትዮጵያ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች አጀብ ላይ ጥቃት ለመፈጸም በመዘጋጀት ላይ እንዳለ ነው ተብሏል።

የአየር ኃይሉ የተዋጊ ሄሊኮፕተር ክንፍ አዛዥ ሻለቃ ደረሰ እንዳለ እንደገለጹት የአልሸባብ የፈንጅ ቡድን በርካታ ፈንጂዎችን ሠራዊቱ በሚንቀሳቀስበት መስመር ላይ በመቅበር ጥቃት ለመሰንዘር አቅደው እየተዘጋጁ ነበር ተብሏል።

የአየር ኃይሎ ኃላፊዎች እንዳሉት በተወሰደው ርምጃ "የአልሸባብ እቅድ ሳይሳካ የፈንጅ ቡድን አባላትን ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ" ሠራዊቱ ያለስጋት እንዲንቀሳቀስ እንዳስቻሉ አመልክተዋል።

አልሻባብ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ፈጸምኩት ስላለው ጥቃት እስካሁን ድረስ ምንም ያለው ነገር የለም።

የኢትዮጵያ ሠራዊት አክራሪውን እስላማዊ ታጣቂ ቡድንን ለመምታት ወደ ሶማሊያ ከገባ 10 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በአፍረካ ሕብረት የሚደገፈውን የሶማሊያ መንግሥትን ለመደገፍ ከሌሎች አገራት ሠራዊት ጋር ሶማሊያ ውስጥ ይገኛል።

አልሻባብ በሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥትና በአገሪቱ በሚገኙ የውጪ ኃይሎች ላይ በመዲናዋ ሞቃዲሾና በሌሎች ስፍራዎች በተለያዩ ጊዜያት የቦንብ ጥቃቶችን በመፈጸም ከባድ ጉዳት እያደረሰ ያለ ቡድን ነው።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከዚህ በፊትም በቡድኑ ላይ ጥቃት በመፈጸም ጉዳት እንዳደረሰ አስታውቋል። የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላኖችም የቡድኑ መስራቾችና መሪዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት በመፈጸም ጉዳት አድርሰዋል።

በቅርቡም አሜሪካ እስላማዊ ቡድን አልሻባብ መስራች አባል የነበረውን ዩሱፍ ጂስ ሶማሊያ ውስጥ በፈጸመችው የአየር ጥቃት መግደሏን ማስታወቋ አይዘነጋም ።