የባህር ዳሩ የኮሮናቫይረስ ህክምና ማዕከል የመሳሪያዎች ጥያቄ

ባህር ዳር

ከአዲስ አበባ ውጪ ለኮሮናቫይረስ ህሙማን ክትትልና የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው የባህር ዳር የመከላከያ ሆስፒታል ለሥራው የሚያስፈልጉ ግብዓቶች እንዲሟሉ ባለሙያዎች ጠየቁ።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የህክምና ባለሙያ ለቢቢሲ እነደገለጹት አሁን በሆስፒታሉ ያሉት ሦስት ታካሚዎች ሲሆኑ እነሱም ጥሩ ሁኔታ ላይ መገኘታቸው ባለው ግብዓት ለመሥራት እንዳስቻላቸው ጠቁመዋል።

ነገር ግን ወረርሽኙ ተስፋፍቶ "10 ወይም 20 ሰው ቢመጣ በዚህ ቁመና መሥራት አንችልም" ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠው በቶሎ ቀድሞ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ማዕከሉ ውስጥ ለኮሮናቫይረስ ህሙማን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የህክምና መሣሪያዎችና ባለሙያዎች ራሳቸውን ከቫይረሱ የሚከላከሉበት ቁሳቁሶች በቁጥር አነስተኛ ናቸው ብለዋል።

ካናገርናቸው ባለሙያዎች መካከል አንዱ "ሜካኒካል ቬንትሌተር የሚበባለው የጽኑ ህሙማን ማሽን አንድ ነው ያለው። የልብ መመርመሪያ ማሽንና ሌሎችም ማሽኖች አልተሟሉም። ለባለሙያዎች መከላከያ የሚውሉ ግብዓቶች የሉም" በማለት ለማሟለት ቸልተኝነት እንዳለ ይናገራሉ።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ምላሽ የሰጡት የክልሉ የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መልካሙ አብቴ፤ አሁን ያለውን ሥራ ለመሥራት የሚያክል በቂ ግብዓት መኖሩን ጠቅሰው የህሙማን ቁጥር ከፍ ካለ ተጨማሪ መሣሪያዎች እንደሚያስፈልጉ አመልክተዋል።

"ይህንን ጉዳይ ከጤና ጥበቃ ሚንስቴር ጋር እየተነጋገርን ነው። ግዢዎችን እየተካሄዱ መሆናቸው ተገልጾልናል፤ ከዚህ በኋላ የሚሰጠን ነው የሚሆነው። እኛምን ባሉን መንገዶች የምናሟላ ይሆናል።"

ከላብራቶሪ መሣሪዎች ጋር ተያይዞም "መመርመሪያዎችን ለማሟላት እየሠራን ነው። ማሽኖችን እያሟላን ነው። አሁን የሚከናወነውን የህክምና ሥራ የሚያስተጓጉል ግን አይደልም" ብለዋል።

ኃላፊው በተጨማሪም የተለየ ተጋላጭነት ላላቸው በባለሙያዎች የጤና ጥበቃ ሚንስቴር የሚገባ ጥቅማ ጥቅምን በተመለከተ እያስጠና መሆኑን ገልጸው በቅርቡ ይፋ ይደረግል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ባህር ዳር በሚገኘው የኮሮናቫይረስ ህክምና በሚሰጥበት ማዕከል ውስጥ ሦስት ታካሚዎች ብቻ ያሉ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት በክልሉ ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የጤና ጥበቃ ሚንስቴር አስታውቋል።