ሰሜን ኮሪያ፡ የኪም ጆንግ-ኡን በጠና ታመዋል የሚለው ዜና የሐሰት ነው ተባለ

ኪም ጆንግ ኡን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ኪም ጆንግ ኡን

የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ-ኡን በጠና ቃመዋል የሚለው ሪፖርት ሐሰት ነው አሉ።

ኪም ጆንግ-ኡን "በጠና ታመዋል"፣ "በሞት እና በህይወት መካከል ይገኛሉ" ወይም "ከቀዶ ህክምና በኋላ እያገገሙ ነው" የሚሉ ዜናዎች ትክክለኛነትን ማረጋገጥ ወትሮም ቢሆን እጅጉን ከባድ ናቸው።

ይሁን እንጂ የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት የ36 ዓመቱ ኪም ጆንግ-ኡን በጠና ስለመታመማሳቸው ከሰሜን ኮሪያ ምንም አይነት ምልክቶች አልታዩም ብለዋል።

የኪም ጆንግ-ኡን ጤናን በማስመልከትም የሚወጡ መሰል ዜናዎች በርካታ መሆናቸውን ተጠቅሷል።

የኪም የጤና መቃወስ ዜና መናፈስ እንዴት ጀመረ?

ከአንድ ሳምንት በፊት ሚያዚያ 7 ኪም ጆንግ ኡን የአያታቸውን የልደት ዝግጅት ሳይታደሙ ቀርተዋል። ይህ በዓል የአገሪቱ መስራች እንደሆኑ የሚታሰቡ ግለሰብ ልደት እንደመሆኑ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ዝግጅት ነው።

ኪም ጆንግ-ኡን ከዚህ ቀደም ሳይታደሙ ቀርተው አያውቅም - ብርቱ ጉዳይ ካልገጠማቸው በቀር አይቀሩም።

ኪም በዝግጅቱ ሳይገኙ መቅረታቸው በበርካቶች ዘንድ እንዴት? ለምን የሚሉ ጥያቄዎች እንዲነሱ አደረጉ።

ኪም ለመጨረሻ ጊዜ በብሔራዊ ጣቢያው የታዩት ሚያዚያ 4 ላይ ነበር። በቴሌቪዥን ሲታዩ እንደተለመደው ዘና ብለው ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ኪም በአደባባይ ሳይታዩ ቀሩ።

ባሳለፍነው ሳምንት ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራ አድርጋ ነበር። የአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ በዘገበበት ወቅት የኪም ጆንግ-ኡንን ስም አልጠቀሰም። ምስላቸውንም አላሳየም። ከዚህ ቀደም ሰሜን ኮሪያ መሰል ወታደራዊ ሙከራዎችን ስታካሂድ ኪም በቴሌቪዥን መስኮት ይታዩ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ,

በአያታቸው የልደት በኣል ላይ ባለመታየታቸው ነበር ወሬው መናፈስ የጀመረው

የኪም በጽኑ የምታመም ዜና

ኪም ጆንግ-ኡን በጽኑ የመታመማቸው ዜና ቅድሞ የተዘገበው ከሰሜን ኮሪያ ሸሽተው መኖሪያቸውን ደቡብ ኮሪያ ባደረጉ ሰዎች በሚመራ እንድ ድረ-ገጽ ላይ ነበር።

'ዴይሊ ኤንኬ' የተሰኘው ድረ-ገጽ አገኘሁት ባለው መረጃ መሠረት የሰሜን ኮሪያው መሪ በልብ ህመም እየተሰቃዩ ይገኛሉ።

ከዚህ በተጨማሪም መገናኛ ብዙሃን ኪም ጆንግ ኡን አብዝተው ሲጋራ በማጨሳቸው፣ ከልክ ባለፈ ውፍረት እና ከሥራ ጫና ጋር ተያይዞ ለልብ ህመም ተጋልጠዋል እያሉ ነው።

ይሁን እንጂ የደቡብ ኮሪያ መንግሥት መግለጫ እና በቻይና ደኅንነት ውስጥ ያሉ ምንጮች ለሬውተርስ እንደተናገሩት የኪም ጆንግ-ኡን ጤና እክል ገጥሞታል መባሉ ስህተት ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስካሁን ድረስ የትኛውም አካል ኪም ጆንግ-ኡን የልብ ቀዶ ህክምና አላደረጉም አላላም።

የደቡብ ኮሪያ መንግሥትም ሆነ የቻይና ደኅንነት ምንጮች ያሉት የሰሜን ኮሪያው መሪ "በጽኑ ታመዋል" የሚለው ዜና ሐሰት ነው።

ኪም ጆንግ-ኡን 'ሲሰወሩ' ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።

እአአ 2014 ላይ ኪም ጆንግ-ኡን ለ40 ቀናት ሳይታዩ ቆይተው ነበር። ይህም በሕዝቡ ዘንድ ኪም ጆንግ-ኡን በተቀናቃኛቸው መፈንቅለ መንግሥት ተከናውኖባቸውዋል የሚል ወሬ በስፋት ተሰራጭቶ ነበር።

ነገር ግን ከዚያ ብዙ ሳይቆዩ ከዘራ ይዘው የሚታዩበት ምስል ላይ ደህና መሆናቸው ለሕዝብ ቀረበ።

ኪም ጆንግ-ኡንን ሊተካ የሚችለው ማነው?

ሰሜን ኮሪያ ውስጥ አንዳች ነገር ቢከሰት ኪም ጆንግ-ኡንን ሊተካ የሚችለው ማን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ኪም ጆንግ-ኡን ከአባታቸው ሞት በኋላ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በአባታቸው ለበርካታ ዓመታት ለስልጣን ሲኮተኮቱ ቆየረተዋል።

ምናልባት ኪም ጆንግ-ኡን አገር ማስተዳደር ባይችሉ፤ የኪም እህት ኪም ዮ-ዮንግ ወንድሟን ልትተካ ትችል ይሆናል። ኪም ዮ-ዮንግ ከወንድሟ ጎን ሆና በወሳኝ ስብሰባዎች ላይ ስትሳተፍ ትታያለች።