ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ በጣለ ከባድ ዝናብ የሰው ህይወት አለፈ

በምስራቅ አፍሪካ በከባድ ዝናብ ምክንያት ጎርፍ ሊያጋጥም ይችላል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, @TV47KE

በከባድ ዝናብ ምክንያት በኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ኡጋንዳ ጨምሮ በሌሎች ምሥራቅ አፍሪካ አገራት የጎረፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊያጋጥም ይችላል ተባለ።

የኬንያ ሜትዮሮሎጂ ክፍል ከባድ ዝናብ መጣሉን ተከትሎ ጎርፍ ሊያጋጥም እንደሚችል አሰጠንቅቋል። ተቋሙ እንዳስታወቀው በዋና መዲናዋ ናይሮቢና በምዕራብና ምሥራቅ የአገሪቷ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ ይጠበቃል ብሏል።

ከትናንት በስቲያ በጋሞ ዞን የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ የአምስት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፋና መዘገቡ ይታወሳል።

በምዕራብ ኬንያ እየጣለ ያለውን ከባድ ዝናብም ተከትሎ ባጋጠመ የመሬት መንሸራተት ቢያንስ ከ10 ሰዎች በላይ ሕይወታቸው አልፏል።

በተመሳሳይ በኡጋንዳም ከባድ ዝናብ እየጣለ መሆኑን ተከትሎ የቪክቶሪያ ሐይቅ መጠን በመጨመሩ በሐይቁ ዳርቻ የሚኖሩ ሰዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ባለፈው እሁድ አሳስበዋል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ክፍልም በጎርፍ ሳቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን ከ10 በላይ ሰዎች ድግሞ ሞተዋል።

ባለፈው ዓመት በህዳርና ታህሳስ ወር ባልተጠበቀ መልኩ የጣለው ከባድ ዝናብ ጎርፍ ማስከተሉ ይታወሳል።

በመሆኑም አሁን እየጣለ ያለው ዝናብም ባልተጠበቀ መልኩ ከባድ እንደሚሆን ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።