ኮሮናቫይረስ፡ ለሕክምና ከሄዱበት ሕንድ መመለስ ያልቻሉ ኢትዮጵያዊያን ችግር ላይ ነን አሉ

ኒው ዴልሂ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, SOPA Images

የምስሉ መግለጫ,

ኒው ዴልሂ ከተማ

በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካዊያን የተሻለ ህክምና ለማግኘት ወደ ሕንድ ይጓዛሉ።

በአሁኑ ሰዓት አገሪቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኘን ለመከላከል ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊየን በላይ ሕዝቧ ከቤት እንዳይወጣ እና ማንኛውም እንቅስቃሴ እንዳይደርግ አግዳለች።

ይህን ተከትሎም ለህክምና ወደ አገሪቱ የሄዱ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው መመለስ ባለመቻላቸው ከባድ ችግር ላይ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ዘውዲቱ ንጉሴ የመቅኔ ንቅለ ተከላ ወይም ‘ቦንማሮ ትራንስፕላንት’ የሚባል ህክምና ለማግኘት ነበር ለሁለት ሳምንታት ወደ ሕንዷ ዋና ከተማ ኒው ደልሂ ያቀናችው።

ዘውዲቱ የደርሶ መልስ የአውሮፕላን ትኬት ብትቆርጥም በሕንድ እንቅስቃሴ እንዳይኖር በመታወጁ ካሰበችው በላይ ለተጨማሪ ቀናት እንድትቆይ ተገዳለች።

"የተወሰነ ገንዘብ ብቻ ነበር ይዤ የመጣሁት፤ ግን የእንቅስቃሴ ገደቡ ከታወጀ በኋላ መንቀሳቀስ ስላልተቻለ ካሰብኩት ጊዜ በላይ በቀን 1000 ሩፒ እየከፈልኩኝ እንድቆይ ተደርጌለሁ ፤ እጄ ላይ ያለው ገንዘብ አልቋል። አላስፈላጊ ወጪ እና እንግልት እየደረሰብኝ ነው" ትላለች።

"አጋጣሚ ሆኖ ለትምህርት የመጡ የማውቃቸው ሰዎች በመኖራቸው አገር ቤት ስሄድ የምከፍላቸው ገንዘብ ሰጥተውኛል" በማለት ስላለችበት ሁኔታ ታስረዳለች።

ከአንድ ቤተሰብ ለህክምና ሦስት ሆነው የመጡ ሌሎች ኢትዮጵያንም አሉ። እህቱንና እና አባቱን ለማሳከም የመጣው ጌታቸው ሹሜ ስላሉበት ሁኔታ፤ “እህቴ በጣም ብዙ መድሃኒት ነው የምትወስደው፤ ለዚያም ደግሞ በቂ ምግብ መመገብ አለባት። እዚህ ያለው ምግብ ብዙም የሚስማማ አይደለም፤ ብዙ መድሃኒት ወስዶ ምግብ አለመመገብ ከባድ ነው” ሲል ይገልጻል።

ሌላኛው ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ታካሚም “ምግብ ለማግኘት በጣም ተቸግረናል። የታሸገ ምግብ ለመግዛት እየፈራን ነው ወደ ውጭ የምንወጣው። ሁኔታው ከቀን ወደቀን እየከበደን ነው። በየቀኑ የቤት ኪራይ ብቻ ነው እያሰላን ያለነው” ሲል በፈተና ውስጥ እንዳሉ ይናገራል።

እነዚህ ታካሚዎች የቀደመ የጤና እክል የነበረባቸው መሆኑ ደግሞ ለኮሮናቫይረስ ያላቸውን ተጋላጭነት ከፍተኛ ያደርገዋል። ይህም ሌላ ጭንቀት ሆኖባቸዋል።

ዘውዲቱ “ያረፍንበት ሆቴል ያን ያህል ግድ ያለው አይደለም፤ ያለው ነገር በጣም የሚያስፈራ ነው። ህክምና ቢያስፈልገን ከሃኪም ቤት መኪና ካልተላከልን በስተቀር መሄድ አንችልም። የምንፈልገውን በቅርበትና በፈለግነው ሰዓት አናገኝም" ትላለች።

ዘውዲቱ ጨምራ "ቢያንስ የመጀመሪያው የእንቅስቃሴ ገደቡ 21 ቀኑ እንዳለቀ ወደ አገር ቤት በረራ ይጀመራል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር ተደጋግፈን ተጋግዘን ነገሮችን እያለፍን የነበረው። በድጋሜ ይራዘማል የሚል በፍጹም አልጠበቅንም። ይሄ ነገር ሲሆን ግን ለእኛ ዱብዳ ነው” ስትል ትናገራለች።

እነዚህ በተለያዩ የሕንድ ግዛቶች በሚገኙ ሆስፒታሎች የሚታከሙ ኢትዮጵያውያን በኒው ዴልሂ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አሳውቀው መልስ እንዳላገኙ ነግረውናል።

ሕንድ ለመጀመሪያ ጊዜ ለ21 ቀናት እንቅስቃሴ እንዳይኖር እገዳ በጣለችበት ወቅት በ56 በረራዎች 10,600 የሚሆኑ የውጭ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አድርጋለች።

ጃፓን፣ ኖርዌይ፣ ጀርመን፣ ሩስያና ፈረንሳይን የመሳሰሉ አገራት በእገዳው ምክንያት ሕንድ የቀሩ ዜጎቻቸውን ካስወጡ አገራት መካከል ናቸው።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ዜጎቹን ወደአገራቸው ለመመለስ ያደረገው ጥረት ካለ በማለት በሕንድ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደውለን ነበር።

ይሁን እንጅ በሃገሪቱ በታወጀው የእንቅስቃሴ እገዳ ምክንያት ኤምባሲው እስከ ቀጣይ ወር ዝግ እንደሆነ ስልካችንን ያነሱ የአገሬው ዜጎች ገልፀውልናል።

በኤምባሲው የሚሰሩ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችም ስለጉዳዩ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኞች አልሆኑም።

በሰሜናዊ ሕንድ የሚኘውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስከያጅ የሆኑትን አቶ ክሩቤል ሽታሁን ግን ስለጉዳዩ፤ “አንዳንድ አገራት በቻርተር በረራ ዜጎቻቸውን እያስወጡ እንደሆነ እናውቃለን። እኛ ግን ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከሕንድ መንግሥት መንገደኛ ለማጓጓዝ የተሰጠን ፈቃድ ስለሌለ ምንም ማድረግ አልቻልንም። ለቻርተር በረራ እኛ እንደዚያ አይነት ጥያቄ አልቀረበልንም። ኤምባሲውም ወደ እናንተ የሚደውሉ ሰዎችን ዝርዝር ስጡን ብለውን ሰጥተናቸዋል። በሕንድ መንግሥት ምንም ዓይነት የኮሜርሻል (ንግድ) በረራዎችን ማድረግ እንዳይቻል ተዘግቷል። የተለየ በረራ ካስፈለገ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሳይሆን በመንገደኞች፣ በአገራት እና በኤምባሲዎች ነው የሚጠየቀው።” ሲሉ በዚህ ምክንያት ዜጎችን ወደ አገር ቤት ለመመለስ እንዳልተቻለ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለያዩ አገራት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መንቀሳቀስ ያልቻሉ አሜሪካዊያንን ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ እያደረገ መሆኑ የሚታወስ ነው።

ባሳለፍነው ሳምንትም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ፤ በቫይረሱ ምክንያት በሌሎች አገራት የነበሩ አሜሪካዊያን ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አገልግሎት መስጠቱን በመጥቀስ ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አሕመድን ማመስገናቸው ይታወሳል።