ኮሮናቫይረስ፡ የዓለም ጤና ድርጅት ሠራተኛ የኮቪድ-19 ናሙና ሲሰበስቡ ተገደሉ

የፓዩ ሶኔ ዊን ማኡንግ አስከሬን በአምቡላንስ ተጭኖ ወደ ሆስፒታል ሲወሰድ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የዓለም ጤና ድርጅት ሹፌር በማይናማር የኮቪድ-19 ናሙና እየሰበሰቡ ሳለ ተገደሉ።

ግለሰቡ ፓዩ ሶኔ ዊን ማኡንግ የሚባሉ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ዓርማን ያነገበ መኪና እያሽከረከሩ እያለ በራክሂኔ ግዛት በተተኮሰባቸው ጥይት መሞታቸው ታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት በመንግሥት ወታደሮችና በአራካን ብሄርተኛ አማፂያን መካከል ሰሞኑን ግጭት ተቀስቅሶ በርካታ ንፁኃን መሞታቸውን ገልጧል።

ሰኞ ዕለት በተገደለው የዓለም ጤና ድርጅት ሹፌር ሞት የማይናማር ወታደሮችም ሆኑ የአራካን አማፂያን እርስ በርስ እየተወነጃጀሉ ይገኛሉ።

የማይናማር ወታደርም ሆነ የአርካን አማፂ በግድያው እጃችን የለበትም ሲሉ አስተባብለዋል።

የማይናማር ወታደር ቃል አቀባይ የሆኑት ማጅ ጄን ቱንቱን ኒይ፣ ጦሩ የተባበሩት መንግሥታትን መኪና የሚያጠቃበት ምክንያት የለውም ብለዋል።

"ለእኛ ለአገራችን ነው የሚሰሩት" በማለት ለሮይተርስ የተናገሩት ቃል አቀባዩ " ለዚያም ኃላፊነት አለብን" ብለዋል።

በማይናማር የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ፅህፈት ቤት የ28 ዓመቱ ሹፌር፣ ሚንብያ ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ በወታደራዊ ፍተሻ ጣቢያ አቅራቢያ መገደሉን ጠቅሶ "እጅጉን ማዘኑን" ገልጿል።

በፌስቡክ ላይ እንደተገለፀው ከሆነ የተባበሩት መንግሥታት ሹፌር የሞተበትና አንድ የመንግሥት ሠራተኛ የቆሰለበት ይህ ጥቃት የደረሰው የአገሪቱ "ጤናና ስፖርት ሚኒስቴርን ለማገዝ" ከሲትዌ ወደ ያንጎን የኮቪድ-19 ቅኝት ናሙና ለመሰብሰብ እየሄዱ ሳለ መሆኑን ገልጾ፣ ጥቃቱን ማን እንደፈፀመ ያለው ተጨማሪ ነገር የለም።

የሹፌሩ አባት ህታይ ዊን ማኡንግ "አዝኛለሁ" በማለት ልባቸው መሰበሩን ተናግረዋል።

"ራሴን ለማረጋጋት እየሞከርኩ ያለሁት ግዳጁን እየተወጣ እያለ መሞቱን በማሰብ ነው" ያሉት አባቱ አክለውም "ማንም ሰው ለመሄድ ፈቃደኛ ባልሆነበት ወቅት በግጭት መካከል ነው የሄደው" ብለዋል።

ዩናይትድ ኪንግደምም ሆነ አሜሪካ ዓለም አቀፉን ወረርሽኝ ለመከላከል እንዲቻል ግጭቱ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

በማይናማር እስካሁን ድረስ 80 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲገለጽ አራት ሰዎች መሞታቸው ተመዝግቧል።

የአራካን አማፂያን ቡድሂስት ሲሆኑ ላለፉት ሁለት ዓመታት ራሳቸውን የማስተዳደር ነፃነታቸው እንዲከበር እየተዋጉ ነው።

አማፂያኑ ለአንድ ወር የተኩስ አቁም ለማድረግ ቢስማሙም መንግሥት ግን ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎታል።