ኮሮናቫይረስ፡ የነዳጅ ዋጋ መውደቅ ምርቱን በነጻ እንድናገኝ ያስችለናል?

የነዳጅ ዘይት ማምረቻ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አሜሪካ የምታመርተው የነዳጅ ዘይት በታሪክ ባልታየ ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋጋው አሽቆልቁሎ ዜሮ ገብቷል። የአሜሪካ የነዳጅ ምርት ማነጻጸሪያ ዋነኛው የዋጋ መተመኛ የምዕራብ ቴክሳስ ተመን እንደሚያመለክተው የአንድ በርሜል ነዳጅ ዘይት ዋጋ ከዜሮ በታች ቁልቁል ወርዷል እየተባለ በመዘገብ ላይ ነው።

ይህም ነዳጅን እየገዙ በሚጠቀሙ አገራት ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች ዘንድ ደስታን የፈጠረ ይመስላል። አንዳንዶች እንዲያውም ኢትዮጵያን የመሰሉ ነዳጅ የማያመርቱ አገራት ምርቱን በነጻ ካልሆነም እየተከፈላቸው እንዲወስዱ ሊደረግ ይችላል የሚል ግምት አሳድረዋል።

ይህ ግን አውነት አይደለም። ታዲያ የአንድ ምርት በተለይም የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከዜሮ በታች ሲወርድ ምን ማለት ነው? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።

በአሁኑ ጊዜ የዓለማችን የነዳጅ ዘይት ፍጆታ በከፍተኛ ደረጃ በመቀነሱ አምራቾች እስከ ግንቦት ድረስ የነዳጅ ማከማቻ ቦታ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል የሚል ስጋት ስላደረባቸው በወደቀ ዋጋ ነዳጁን እንዲወስዱላቸው እየለመኑ ነው ማለት ይቻላል።

ይህም ማለት ነዳጅ አምራቾች ምርታቸውን ለመሸጥ ካለመቻላቸው በተጨማሪ ያመረቱትን ለማጠራቀም የሚሆን ስፍራ ለመከራየት በመገደዳቸው ከገቢ ይልቅ ወጪው በዝቶባቸዋል። ይህም ሆኖ የነዳጅ ዋጋ በዓለም ላይ ዝቅ እያለ ቢሆንም ፍጆታው ከመጨመር ይልቅ እየቀነሰ ነው። ስለዚህ ምርቱ ፈላጊ አጥቷል ማለት ነው።

በአፍሪካ አገራትም ውስጥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክስተትን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ቢቀንስም ፍጆታው ሊያድግ ይቀርና ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ የሚውለውን ያህል የሚገዛ አልተገኘም።

በአጠቃላይ በበርካታ የአፍሪካ አገራት ውስጥ በበሽታው ምክንያት የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብን ተከትሎ የነዳጅ ፍጆታው ስለቀነሰ ፍላጎቱ እያሽቆለቆለ መሆኑ ተነግሯል።

ለምሳሌም የአውሮፕላን ትራንስፖርት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፣ ፋብሪካዎች የምርታቸውን መጠን ቀንሰዋል አሊያም አቁመዋል፤ እንዲሁም በከተማና በአገር አቋራጭ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚጠመዱት ተሽከርካሪዎች ከእንቅስቃሴ ተቆጥበዋል። በዚህም የነዳጅ ፍላጎት አሽቆልቁሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ስለዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ከየትኛውም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ አንጻር የነዳጅ ፍጆታ ይጨምራል የሚል ግምት ለአሁኑ በቅርበት አይታይም።

በአሁኑ ጊዜ ምንም እንኳን የነዳጅ ዋጋ ቢወርድም የማምረት ሂደቱ ግን ቀጥሏል። ለዚህም ምክንያቱ የነዳጅ ማውጫ ጉድጓዶችን ከመዝጋት ይልቅ ነዳጁን እያመረቱ ለምርት ማጠራቀሚያ ቦታ ኪራይ መክፈል አዋጪ በመሆኑ ነው።

መቀመጫቸውን ኬንያ ያደረጉት በነዳጅ ዘይት ዙሪያ በግል የሚያማክሩት ፓትሪክ ኦባት እንደሚሉት "በአሁኑ ጊዜ የሚታየው ነዳጅ አምራቾች ምርታቸውን መሸጥ አልቻሉም፤ በተጨማሪ ደግሞ ነዳጁን ለሚያከማቹበት ቦታ መክፈል አለባቸው። ስለዚህም ነዳጅ ማውጫዎችን ከመዝጋት ወጪ እያወጡ በምርታቸው መቀጠልን መርጠዋል። ለዚህ ነው በዋጋ ላይ ከዜሮ በታች የሆነ ውጤት የሚታየው" ብለዋል።

ስለዚህም የዋጋው መውደቅ ምርቱን ለፈላጊው በነጻ የማግኘት ዕድልን የሚፈጥር ሳይሆን፤ አምራቹ ላይ የተፈጠረውን የወጪ ጫና ለማመልከት ነው። በቀላል ምሳሌ ነዳጅ አምራቹ ምርቱን የያዘውን በርሜል ከመሸጥ ይልቅ ምርቱን ለማጠራቀም የሚሆን ቦታን ለመከራየት የሚያወጣው ወጪ ነው ዋጋው ላይ ትልቅ ለውጥ ያሳየው።

ስለዚህ ማንም ነዳጅ ዘይትን በነጻ ሊያገኝ አይችልም። በአሁኑ ጊዜ ገበያው ምላሽ እየሰጠ ያለው በዓለም ዙሪያ ላለው የነዳጅ ፍላጎት ማሽቆልቆልና በወረቀት ላይ ለሚታየው ዋጋ ነው።

ይህ በዚህ ከቀጠለ በየብስ ላይ የሚገኙት የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች ሞልተው በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የውሃ አካላት ላይ በሚንቀሳቀሱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ሳይቀር ማከማቸት ሊቀጥል ይችላል፥ እስከዚያም ያለው ሁኔታ ተስተካክሎ እንቅስቃሴው ወደነበረበት ሊመለስና የነዳጅ ፍጆታውም ከምርቱ ጋር በተቀራረበ ሁኔታ ሊስተካከል ይችላል።

"ምንም እንኳን የተትረፈተፈ ምርት ቢኖርም ማምረቱ ቀጥሏል በዚህም ምክንያቱ ዋጋው የበለጠ ማሽቆልቆሉ አይቀርም። በቀጣዮቹ ወራት የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ ከ15 እስከ 20 ዶላር ይሆናል" ሲሉ ኦባት ተንብዋል።

ናይጄሪያና አንጎላን የመሳሰሉ የምጣኔ ሃብታቸው ከነዳጅ ዘይት ምርት ጋር የተቆራኘ የአፍሪካ አገራት ከባድ ጫና ይገጥማቸዋል ተብሎ ይገመታል። ከሌሎች ጋር ተወዳድረው ምርታቸውን በበርሜል እስከ 10 ዶላር መሸጥ ከቻሉ እድለኞች ሊባሉ ይችላሉ ተብሏል።