ሳኡዲ አረቢያ ባለፈው ዓመት 184 ሰዎችን በሞት ቀጥታለች- አምነስቲ

ተቃዋሚ ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, ANADOLU AGENCY

የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ አምነስቲ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሞት ቅጣት የቀነሰ ቢሆንም ሳኡዲ አረቢያ ባለፈው ዓመት ብቻ ከፍተኛ ነው የተባለውንና 184 ሰዎችን በሞት መቅጣቷን አስታወቀ፤ ይህም በአገሪቷ ታሪክ ከፍተኛው ነው ተብሏል።

በኢራቅም የሞት ቅጣቱ ቀድሞ ይፈጸም ከነበረው በእጥፍ በልጦ ባለፈው ዓመት ቁጥሩ 100 ደርሷል፤ ኢራን 251 ሰዎች በሞት በመቅጣት ቻይናን ተከትላ ሰዎች በሞት የምትቀጣ ሁለተኛዋ አገር ሆናለች።

ሪፖርቱ እንደሚያሳየው በዓለም አቀፍ ደረጃ በሞት የሚቀጡ ሰዎች ቁጥር ለአራት ተከታታይ ዓመታት ወደ 657 ዝቅ ብሏል፤ ይህም በአውሮፓዊያኑ 2018 ከነበረው 5 በመቶ ቀንሷል።

እንደ አምነስቲ ከሆነ ቁጥሩ ባለፈው አስር ዓመታት ከተመዘገበው ዝቅተኛው ነው።

የሰብዓዊ መብት ቡድኑ በቻይና የሚፈጸመው የሞት ቅጣት በሺዎች የሚቆጠርና የመንግሥት ሚስጢር ነው ተብሎ ስለሚታመን የቻይናን አሃዝ አላካተተም።

ኢራን፣ ሰሜን ኮሪያ እና ቬትናንም ጨምሮ ሌሎች አገራትም መረጃን የማግኘትን እድል ውስን በማድረግ የሚፈጽሙትን የሞት ቅጣት ትክክለኛ ቁጥር ደብቀዋል ብሏል።

"የሞት ቅጣት በጣም አጸያፊና ኢሰብዓዊ ድርጊት ነው፤ ከእስር ያለፈ ቅጣት የሚያስጥል ወንጀልን የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃም የላቸውም፤ አብዛኞቹ አገራት ይህንን ተረድተዋል፤ በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃም የሞት ቅጣት መቀነሱ አበረታች ነው፤" ሲሉ በአምነስቲ ከፍተኛ የጥናት ዳይሬክተር የሆኑት ክሌር አልጋር ተናግረዋል።

ዳይሬክተሯ በሳኡዲ አረቢያ የሚፈጸመው የሞት ቅጣት ማሻቀቡ ግን አንቂ ደወል ነው ብለዋል።

ባለፈው ዓመት ሳኡዲ አረቢያ 178 ወንዶችና ስድስት ሴቶችን በሞት ቀጥታለች፤ ከእነዚህ መካከል ግማሽ ያህሉ የውጭ አገር ዜጎች ናቸው። በ2018 ቁጥሩ 149 ነበር።

አብዛኞቹ የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው ከአደንዛዥ እጽ ዝውውር እና ግድያ ወንጀል ጋር በተያያዘ ነው። ይሁን አንጂ አምነስቲ የሞት ቅጣት በአገሪቷ የጨመረው በተቃዋሚ የሺአ ሙስሊም ማኅበረሰቦች ላይ እንደ ፖለቲካ መሳሪያ እየተጠቀሙበት እንደሆነ መረጃ እንዳለው አስታውቋል።

በኢራቅም የሞት ቅጣት በ2018 ከነበረው 52 ባለፈው ዓመት 100 መድረሱ የሚያስደነግጥ ነው ብለዋል ዳሬክተሯ።

የቁጥሩ መጨመር በእስላማዊ የጂሃዲስት ቡድን አባል ናቸው በሚል ምክንያት በግለሰቦች ላይ የሞት ቅጣት መጣሉ በመቀጠሉ እንደሆነ ክሌር አስረድተዋል።

በደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት ባለፈው ዓመት ብቻ በትንሹ 11 ሰዎችን በሞት ቀጥተዋል። ይህ ቁጥር አገሪቷ ራሷን ማስተዳደር ከጀመረችበት 2011 በኋላ ከፍተኛው ነው ተብሏል።

የመን ባለፈው ዓመት በትንሹ 7 ሰዎችን በሞት ቀጥታለች፤ በ2018 ከነበረው ጋር ሲነጻጸርም በሦስት ጨምሯል።

ባህሬንና ባንግላዴሽን በአንድ ዓመት ከቆመ በኋላ የሞት ቅጣት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።

አምነስቲ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁጥሩ ለመቀነሱ በርካታ ምክንቶች መኖራቸውን ይገልጻል።

የሞት ቅጣትን በከፍተኛ ሁኔታ በሚፈጽሙት በግብጽ፣ በጃፓን እና በሲንጋፖር ውስጥ መቀነስ አሳይቷል።

በኢራንም በ2017 ጸረ አደንዛዥ እጽ ሕግ ካጸደቀች በኋላ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የሞት ቅጣት የሚፈጸምባቸው ሰዎች ቁጥር ቀንሷል።

በአፍጋኒስታን ከ2010 አንስቶ አንድም የሞት ቅጣት አልተፈጸመም፡፡ በታይዋንና ታይላንድ ቅጣቱ ጋብ ያለ ቢሆንም በ2018 ግን ቅጣቱን ፈጽመዋል።

አምነስቲ እንዳለው በዓለም አቀፍ ደረጃ 106 አገራት ለሁሉም የወንጀል ዓይነቶች የሞት ቅጣትን ከሕጋቸው ውስጥ የፋቁ ሲሆን 142 አገራት ደግሞ በሕግ ወይም በተግባር የሞት ቅጣትን አስወግደዋል።