ኮሮናቫይረስ፡ በርካታ ሰዎች ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ እየተሻገሩ መሆኑ አሳሳቢ ሆኗል

ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የጭነት መኪኖች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የጭነት መኪናዎች ጸረ ተዋህሲያን ይረጫሉ

በርካታ ሰዎች በኮረናቫይረስ ከተያዙባት ጎረቤት አገር ጂቡቲ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ፤ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የአፋርና አማራ ክልሎች ጥረት እያደረጉ መሆኑን አመለከቱ።

የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ያሲን ሙስጠፋ ለቢቢሲ፤ "ከጅቡቲ ከበሽታው የሚሸሹ እንዲሁም ጾም ስለሆነ ሙቀቱን ለማሳለፍ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ በርካታ ሰዎች አሉ" ብለዋል።

መንግሥት የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመቆጣጠር በድንበሮች በኩል የሰዎች እንቅስቃሴን ቢያግድም ከጂቡቲ "የሚገቡት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው" ይላሉ ኃላፊው።

አንድ ሚሊዮን የማይሞላ ሕዝብ ያላት ጂቡቲ አንድ ሺህ የሚጠጉ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን በግዛቷ ውስጥ ማግኘቷን ተከትሎ ድንበር እየተሻገሩ በሚገቡ ሰዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ መጀመሩ ተገልጿል።

ከጅቡቲ በአፋር ክልል በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገቡ አስራ አምስት የመግቢያ በሮች ሲኖሩ ሦስቱ ዋና የሚባሉ መሆናቸውን ያመለከቱት ኃላፊው በሁሉም ላይ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከአፋር ክልል ጋር ወደሚዋሰነው የአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ከጅቡቲ በኩል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የዞኑ የጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ካሊድ ሙስጠፋም ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ሰዎቹ በእግር ድንበር ተሻግረው የሚገቡባቸው የተለያዩ ቦታዎች መኖራቸውን አመልክተው "አንዱ ባቲ ወረዳ ነው። ባቲ ላይ አቢላል የሚባል ቦታ በተለይ በእግርና በመኪና ሰዎች ስለሚገቡ የሙቀት ልኬት ጀምረናል" ሲሉ የበሽታው ምልክቶችን ለመለየት እየሞከሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ካሉት ሰባት ወረዳዎች አምስቱ ከአፋር ክልል ጋር ስለሚዋሰኑ "ከጅቡቲ በአፋር በኩል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በርካታ በመሆኑ አራቱ ወረዳዎች ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የስጋት ቀጠና ናቸው በሚል ተለይተዋል" ሲሉ የዞኑ ጤና ኃላፊ አቶ ካሊድ አመልክተዋል።

በአፋር ክልል "18 የለይቶ ማቆያ ስፍራዎች ተዘጋጅተዋል" ያሉት የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ በተለይም ደግሞ በሦስቱ ዋና ዋና መግቢያዎች በኩል ብዛት ያላቸው ሰዎች በመኪናና በእግር ስለሚገቡ ትኩረት መደረጉን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

እስካሁንም የአፋር ክልል መንግሥት ከጅቡቲ የሚመጡ ሰዎችን ለመቆጣጠር እያከናወነ ባለው ሥራ ወደ ለይ 380 የሚሆኑ ሰዎች ወደ ለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲገቡ መደረጉንና ከለይቶ ማቆያ ለመውጣት የሚሞክሩ በመኖራቸው ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ጨምረው ገልፀዋል።

በጅቡቲ በሽታው ከፈጠረው ስጋትና በአሁኑ ወቅት ካለው ሞቃት የአየር ሁኔታ ለመሸሽ ድንብር አልፈው የሚመጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የሚሄድ ከሆነ ለዚሁ ተብሎ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ ወደተዘጋጀው የለይቶ ማቆያ እንዲዛወሩ እንደሚደረግ አቶ ያሲን ለቢቢሲ ጨምረው አስረድተዋል።

በአፋር ክልል እስካሁን አንድ ሰው በኮሮናቫይረስ መያዙ ተረጋግጧል፤ በክልሉ የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ቤተ ሙከራ በሚቀጥለው ሳምንት ሥራ ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተው አሁን ግን ናሙናዎች ወደ አዲስ አበባ ተልከው እንደሚመረመሩ ኃላፊው ገልፀዋል።

በአገሪቱ በተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት የድንበር መግቢያዎች ዝግ ቢሆኑም ከጂቡቲ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንን መመለስ እንደማይቻል ያመለከቱት ኃላፊው ነገር ግን "ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ ተደርገው ከተመረመሩ በኋላ ነጻ መሆናቸው ሲረጋገጥ ይወጣሉ" ብለዋል።

በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 117 የደረሰ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከጂቡቲ መጥተው በድሬዳዋ ለይቶ ማቆያ የሚገኙ ሰዎች እንደሚገኙበት የጤና ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።

ጂቡቲ ከ980 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የተረጋገጠ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሁለቱ ሞተዋል። በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ የጨመረው በአንድ ሳምንት ውስጥ ነው።

ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ መከላከያ ኃይል በጅቡቲ ባሉት ወታደራዊ የጦር ሰፈሮች በአጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ አውጇል።

ድንብር ተሻጋሪ የሰዎች እንቅስቃሴን ለመቆጠጠር በሚደረገው ጥረት ውስጥ 'ዳጉ' የተባለውን የአፋር ማኅበረሰብ ባህላዊ የመረጃ መለዋወጫ መንገድን እየተጠቀሙ መሆናቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ምክልት ኃላፊ አቶ ያሲን አመልክተዋል።

የማኅበረሰቡ አባላት ጂቡቲ ውስጥ እየተስፋፋ ስላለው ወረርሽኝ ትኩረት አድርገው መረጃ እንደሚለዋወጡ "በየጊዜው ለእኛም ሪፖርት ያደርጋሉ። መረጃውን እየተለዋወጡ ስለሆነ እኛን በጣም እየጠቀመን ነው" በማለት ተናግረዋል።

በእግር ድርበር አቋርጠው የሚገቡትንም ከፀጥታ ኃይሉ በተጨማሪ ኅብረተሰቡ እየተከታተለ እንደሚጠቁም ገልጸው "ሕዝቡ ከጂቡቲ የሚመጡ ንክኪ ይኖራቸዋል በሚል ዘመዶቻቸውን ጭምር ወደ እኛ ያመጧቸዋል፤ ይሄም ለሥራችን አጋዥ ሆኗል" ብለዋል።

ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መኪኖችም ጋላፊ ላይ ጸረ ተዋህሲያን እንደሚረጩና የከባድ መኪኖች አሽከርካሪዎችም ሲገቡና ሲወጡ አስፈላጊውን በሽታውን የመከላከያ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይደረጋል ብለዋል ኃላፊው።