ኮሮናቫይረስ፡ 'ሪቬንጅ ፖርን' ለተሰኘው ተቋም ጥቆማ የሚሰጡ በርክተዋል

'ሪቬንጅ ፖርን' ለተሰኘው ተቋም ጥቆማ የሚሰጡ በርክተዋል

ሪቬንጅ ፖርን ሄልፕላይን የተሰኘ የእንግሊዝ ተቋም በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሰዎች ቤታቸው መሰንበት ከጀመሩ ወዲህ የሚደርሱት ጥቆማዎች እጥፍ መሆናቸውን አሳውቋል።

በመንግሥት ገንዘብ የሚንቀሳቀሰው ይህ ተቋም ሰዎች ቤት ውስጥም ሆነ በማሕበራዊ ድር-አምባዎች የሚደርስባቸውን ጥቃት ለማስቆም ይተጋል።

ቀስቃሾች ድርጅቱ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ከመንግሥት እንዲበጀትለት አቤት እያሉ ነው። ድርጅቱ አሁን ሁለት ቋሚ ሠራተኞች ብቻ ነው ያሉት።

የደርሃም ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሯ ክሌር ማክግሊን ጥቃት ማለት ቤት ውስጥ የሚፈፀም ብቻ አይደለም ይላሉ። ሰዎች በማሕበራዊ ድር-አምባዎችም ሆነ በድረ-ገፅ ጥቃት ሊደርስባቸው ይችላል።

አልፎም ጭንቀት፣ ፍቺ እና ሥራ ማጣት ሰዎች ፀባያቸው እንዲቀያየርና ሌሎች ሰዎች ላይ ጥቃት እንዲያደርሡ ምክንያት ሊሆን ይችላል፤ ለዚህ ነው ሁለቱንም ወገኖች የምንረዳው ይላሉ።

ሰዎች ቤታቸው ውስጥ መዋላቸው የበለጠ ስልካቸው ላይ ጊዜ እንዲያጠፉና ማሕበራዊ-ድር አምባዎች ላይ ተተክለው እንዲውሉ እያደረጋቸው ነው።

የድርጅቱ መሪ የሆኑት ሶፊ ሞርቲመር፤ ከግማሽ በላይ የሚደርሷቸው ጥሪዎች የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ያሉ ሰዎች መሆናቸውን አሳውቀው፤ ብዙዎች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው ይላሉ።

«ይህ በቀላል ልናየው የሚገባ ጉዳይ አይደለም። የሚድርሱን ጥሪዎች ምን ያክል የሰቀቀን ድምፅ እንዳለባቸው መናገር ያዳግታል። አልፎም ብዙዎች ራሳቸውን ሊጎዱ ወይም የራስ ማጥፋት እሳቤ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ።»

ባዶ ቤት በክረምት

የ21 ዓመቷ ኢቫ አንድ የፅሑፍ መልዕክት ሲደርሳት መሬት ተከፍታ ብትውጣት ተመኝታ ነበር። «የራቁት ፎቶዎችሽን ለሕዝብ ስበትን በጣም ደስ እያለኝ ነው። ሰዉም 'ፀያፍ' መሆንሽን ያኔ ያውቃል» ይላል አጭር የፅሑፍ መልዕክቱ።

ወዲያው ጭንቅላቷ ውስጥ የመጣው የቀድሞ ፍቅረኛዋ ነው። ከአዲሱ ፍቅረኛዋ ጋር አንድ ቤት ውስጥ መኖሯ እንደማያስደስተው ታውቃለች። ለሁለት ዓመት ከቀድሞ ፍቅረኛዋ ጋር ስትሆን የተነሳቻቸው ፎቶዎችና ቪዲዎች በእጁ አሉ።

በወቅቱ አልቅሳ ልታባራ እንዳልቻለች እና በድንጋጤ ምክንያት እጅግ ተሸብራ እንደነበር ትናገራለች።

ኢቫና የቀድሞ ጓደኛዋ አንድ መሥሪያ ቤት ነው የሚሠሩት። ይህ ማለት ደግሞ የደረሰባትን ለአለቃዋ መናገር አለባት። ለቤተሰቦቿም ጭምር። የቀድሞ ጓደኛዋ ጨክኖ ፎቶዎቹን ያጋራል የሚል እምነት ባይኖራትም ብቻውን ቤት ውስጥ መሆኑ ለክፉ ሐሳብ ሊያጋልጠው እንደሚችል ታስባለች።

ክስ. . .

ባለፉት አራት ሳምንታት ብቻ ሪቬንጅ ፖርን ሄልፕላይን 200 ክሶች ከፍቷል። ከተከፈተ ወዲህ እንዲህ ያለ በርካታ ክስ ሲከፍት የመጀመሪያው ነው።

በርካቶቹ በዝባዦች እንዲሁም ብዝበዛ የሚድርስባቸው ከ18 ዓመት በታች ያሉ ናቸው።

ሪቬንጅ ፖርን ሄልፕላይን ብቻ ሳይሆን በርካታ የበይነ-መረብ ጥቃትን የሚከላከሉ ተቋማት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ ጥቃቶች ማስተዋላቸውን ይናገራሉ። መሰል ጥቃቶች እንግሊዝ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም እየተስተዋሉ እንደሆነም ነው እኒህ ድርጅቶች ያገኙት መረጃ የሚያሳየው።

ብዙ ሃገራት ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በበይነ-መረብ የሚደርሱ ጥቃቶችን በሕግ የሚያስቀጡ እንዲሆኑ እያደረጉ ነው።

'ጥቃት ቢደርስብኝ ምን ላድርግ?'

  • የደረስብዎን ጥቃት ይመዝግቡ። በይነ-መረብ [ኢንተርኔት] ላይ ጥቃት ከደረስብዎ ለማስረጃ ሊያገለግል ስለሚችል ይያዙት።
  • ፎቶው ወይም ቪድዮ ለተለጠፈበት ድረ-ገፅ ያሳውቁ [ሪፖርት ያድርጉ]
  • ለቅርብ ጓደኛዎ ወይም ለቤተሰብ ይናገሩ