ፌስቡክ በአንድ ጊዜ 50 ሰዎች ጋር የሚደውሉበት ቴክኖሎጂ ይዞ መጥቷል

አዲሱ ቴክኖሎጂ

የፎቶው ባለመብት, FACEBOOK

ፌስቡክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰዎች በቪድዮ ጥሪ መገናኘት ማብዛታቸውን ተከትሎ በዋትስአፕና ሜሴንጀር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ይዞ ብቅ ብሏል።

'ሜሴንጀር ሩምስ' የተባለው የመልዕክት መላላኪያን ተጠቅመው ለ50 ሰዎች የቪድዮ ጥሪ ማድረግ ይችላሉ።

ኩባንያው ለቢቢሲ እንደተናገረው አዳዲሶቹ ለውጦት ከታሰበላቸው ጊዜ በፊት ቀድመው ይፋ የሆኑት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ነው።

የማርክ ዙከርበርግ ድርጅት ሰዎች ሳይጋበዙ ወደ ቪድዮ ጥሪዎቹ እንዳይመጡ የሚከላከል መላም አበጅቷል።

አዳዲሶቹ ቴክኖሎጂዎች ከአርብ ጀምሮ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ላሉ ተጠቃሚዎች ክፍት ሲሆኑ ለሁሉም የፌስቡክ ተጠቃሚ ለማድረስ ሳምንታት ሊወስድ ይችላል ተብሏል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ የቪድዮ ጥሪ መተግበሪያዎች የገበያ ፀሐይ ወጥቶላቸዋል። ፌስቡክ እንደሚለው በሜሰንጄር አማካይነት የሚካሄዱ የቪድዮ ጥሪዎች ከባለፈው ዓመት እጥፍ ጨምረዋል።

የፌስቡክ ተቀናቃኙ ዙም የሰተኘው የቪድዮ ጥሪ መተግበሪያ በአንድ ቀን እስከ 300 ሚሊዮን ደንበኞች እያስተናገደ እንደሆነ ይናገራል።

ለወትሮው መሰል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ሕዝብ በሞላው አዳራሽ ይፋ የሚያደርገው ፌስቡክ አሁን ግን በአለቃው ማርክ ዙከርበርግ አማካይነት በድረ-ገፅ ለማሳወቅ ተገዷል።

የቪድዮ ጥሪ የሚደርሳቸው ሰዎች ወደ ጥሪው በፈለጉት ሰዓት መግባትም ሆነ መውጣት ይችላሉ። ኩባንያው ይህንን ቴክኖሎጂ በዋትስአፕና ኢንስታግራም ላይም ሊተግብር እንደሆነ አሳውቋል።

ዋትስአፕ ላይ የነበረው ለአራት ሰው ብቻ የሚደረግ የቪድዮ ጥሪ ወደ ስምንት አድጓል። ፌስቡክ ላይ ደግሞ ቀጥታ ሥርጭት የሚያካሂዱ ሰዎች ከሌሎች ጋር መግባት እንዲችሉ ሆኗል። ኢንስታግራም ላይቭ የተሰኘው ዘዴ ደግሞ በዴስክቶፕ እውን እንዲሆን ተደርጓል።

የሙከራ ሥርጭቶች በርካታ የሜሴንጀር ተጠቃሚዎች ባሉባቸው አርጀንቲናና ፖላንድ የተካሄዱ ሲሆን ለሙከራው እስከ 20 ሰው ድረስ እንዲሳተፍ ተደርጓል።

ፌስቡክ ይህንን ቴክኖሎጂ ሲያብላላ ከሌሎች መሰል ቴክኖሊጂዎች ልምድ እንደቀሰመ አምኗል።