ከኮሮናቫይረስ ለማገገም ምን ያክል ጊዜ ሊወስድብዎ ይችላል?

የዓለም የጤና ድርጅት ከ20 ሰዎች አንድ ሰው ወደ ፅኑ ሕሙማን ክፍል ይገባል ይላል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኮቪድ-19 ባለፈው ታህሳስ የተከሰተ ወረርሽኝ ነው። ነገር ግን ለአንዳንድ በሽተኞች ከቫይረሱ ለማገገም ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል።

የአንድ ሰው የማገገም ሂደት በበሽታው ምን ያህል ተጠቅቷል የሚለው ላይ የተመረኮዘ ነው። አንዳንድ ሰዎች ከሽታው ወዲያውኑ ሊድኑ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ የበሽታው ስቃይ አብሯቸው ሊዘልቅ ይችላል።

ዕድሜ፣ ፆታ እንዲሁም ሌሎች ነገሮች ሰዎች በበሽታዎች የመጠቃት ዕድላቸወን ሊወስኑ ይችላሉ።

መካከለኛ የህመም ስሜት ብቻ ከሆነ ያለኝስ?

ኮቪድ-19 የያዛቸው በርካታ ሰዎች መካከለኛ የህመም ስሜት ያዳብራሉ - እነዚህ ምልክቶች ሳልና ትኩሳት ናቸው። አልፎም ሰውነት ማሳከክ፣ ድካም፣ ጉሮሮ ማሳከክ እና የራስ ምታት ሊያጋጥማቸው ይችላል።

ሳል መጀመሪያ ሲጀመር ደረቅ ያለ ነው። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ አክታ የተቀላቀለበት ይሆናል። አክታው ቫይረሱ የገደላቸው የሳንባ ሴሎችን ይዞ ይወጣል።

እነዚህ ምልክቶች በቂ እረፍት በማድረግ፣ ፈሳሽ በመጠጣትና በፓራሲታሞል ክኒን ማከም ይቻላል።

መካከለኛ የህመም ስሜት ያላቸው ሰዎች በቀላሉ ሊያገግሙ ይችላሉ። የዓለም ጤና ድርጅት ትኩሳቱ ቶሎ ሊለቅ ይችላል፤ ሳሉ ግን ትንሽ ሊቆይ ይችላል፤ በአጠቃላይ ግን በሁለት ሳምንት ውስጥ ሊያገግሙ ይችላሉ ይላል።

ከበድ ያለ የህመም ምልክት ካለብኝስ?

አንዳንድ ሰዎች ከበድ ያለ ሕመም ሊያጋጥማቸው ይችላል። ቫይረሱ ከያዛቸው በ10 ቀናት ውስጥ ከበድ ያሉ ምልክቶች ሊያሳዩ ይችላሉ።

ለውጡ ድንገተኛ ሊሆን ይችላል። መተንፈስ አዳጋች ይሆናል። ይህ የሚሆነው የሰውነት መከላከል አቅም ከቫይረሱ ጋር በሚያደርገው ትግል ምክንያት ነው። አንዳንድ ሰዎች ሆስፒታል ገብተው ኦክስጂን ሊያስፈልጋቸው ይችላል።

አጠቃላይ ሐኪሟ ሳራህ ጃርቪስ «የትንፋሽ እጥረት እስኪስተካከል ጊዜ ሊወስድ ይችላል» ይላሉ። ሐኪሟ ቢያንስ ስምንት ሳምንታት ሊወስድ እንደሚችል ይጠቁማሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፅኑ ሙማን ክፍል መግባት ቢኖርብኝስ?

የዓለም የጤና ድርጅት ከ20 ሰዎች አንድ ሰው ወደ ፅኑ ሕሙማን ክፍል ገብቶ በማደንዘዣና ቬንቲሌተር መታከም ሊኖርበት ይችላል ይላል። ከፅኑ ሕሙማን ክፍል ከወጡ በኋላ ወደ መደበኛ መታከሚያ ይወሰዳሉ።

ከፅኑ ሕሙማን ክፍል የሚወጡ ሰዎች እስከ 18 ወራት የማገገሚያ ጊዜ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ነገር ግን ከዚህም ባነሰ ወቅት ሊያገግሙ የሚችሉ ሰዎች ይኖራሉ።

ቫይረሱ የዘለቄታ ጤና ላይ ያለው ጉዳትስ?

ኮሮናቫይረስ በዘለቄታዊ ጤና ላይ ያለው ጉዳት አልተለየም። ነገር ግን አንዳንድ ጠቋሚ ክስተቶች የሚያሳዩትን ተመርኩዞ መገመት ይቻላል ይላሉ ባለሙያዎቹ።

'አርድስ' የተሰኘ የመትንፈሻ አካላትን የሚያጠቃ በሽታን ተከትሎ ሳንባ ሊጎዳ ይችላል።

ሌላኛው የጤና ባለሙያዎች የሚመክሩት ነገር በሽተኞች የአእምሮ ጤናቸውንም እንዲታዩ ነው። ምክንያቱም ሆስፒታል ውስጥ አእምሮ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉና።

ሌላኛው ደግሞ ድካም ነው። መካከለኛ ምልክት ያሳዩ ሰዎች እንኳ ረዘም ላለ ጊዜ የድካም ስሜት ላይለቃቸው ይችላል።

የጆንስ ሆፕኪስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ እንደሚያሳየው እስከዛሬ [ሚያዝያ 17/2012] ድረስ ከ2.8 ሚሊዮን የኮሮናቫይረስ ታማሚዎች መካከል 795 ሺህ ያህል ሰዎች አገግመዋል። ይህ ይፋዊ መረጃ ይሁን እንጂ ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል ይነገራል።

ኮቪድ-19 ድጋሚ ሊይዘኝ ይችላል?

ኮቪድ-19 ድጋሚ ሊይዝ እንደሚችል በሰፊው ቢነገርም ምንም ማረጋገጫ አልተገኘም። በሽተኞች ቫይረሱን ተዋግተው ካሸነፉ ከዚያ በኋላ የመከላከል አቅማቸው ሊዳብር እንደሚችል ይታመናል።

ድጋሚ ተይዘዋል ተብለው የታሰቡ ሰዎች ምናልባትም የምርመራ ስህተት አጋጥሞ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።