የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ታዩ

ኬሲኤንኤ የተሰኘው ብሔራዊ ጣብያ እንደዘገበው ዕለተ አርብ የሰሜን ኮሪያው መሪ በአንድ የማዳበሪያ ፋብሪካ ምርቃት ላይ ተገኝተዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ኬሲኤንኤ የተሰኘው ብሔራዊ ጣብያ እንደዘገበው ዕለተ አርብ የሰሜን ኮሪያው መሪ በአንድ የማዳበሪያ ፋብሪካ ምርቃት ላይ ተገኝተዋል

ኪም ጆንግ ኡን ከ20 ቀናት በኋላ በአደባባይ ታይተዋል ሲል የሰሜን ኮሪያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘገበ።

ኬሲኤንኤ የተሰኘው ብሔራዊ ጣቢያ እንደዘገበው ዕለተ አርብ የሰሜን ኮሪያው መሪ በአንድ የማዳበሪያ ፋብሪካ ምረቃ ላይ ተገኝተዋል። ጣቢያው አክሎም ፋብሪካው ውስጥ የነበሩ ሰዎች መሪያቸውን ሲያዩ በጭብጨባና ጩኸት ተቀብለዋቸዋል።

ኪም ጆንግ ኡን ለመጨረሻ ጊዜ በቴሌቪዥን የታዩት ከ20 ቀናት በፊት ነበር። ይህንን ተከትሎም ዓለም ሳይሞቱ አልቀሩም እያለ ሲያወራ ከርሟል።

የሰሜን ኮሪያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን አሉ ይበል እንጂ እውነታውን ማጣራት አልተቻለም። ጣቢያው ኪም በመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ጥብጣብ ሲቆርጡ የሚያሳዩ ፎቶዎችን ለቋል።

ስለ ኪም ከሚድያ መጥፋት የተጠየቁት ዶናልድር ትራምፕ ለጊዜው በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት አልሻም ብለው ነበር።

የኮሪያ ማዕከላዊ ዜና ወኪል [ኬሲኤንኤ] እንዳለው ኪም፤ እህታቸውን ጨምሮ በተለያዩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ታጅበው ነበር።

"የሰሜን ኮሪያው መሪ ሰሜን ፒዮንግያንግ በሚገኝ በአንድ ፋብሪካ ተገኝተው ጥብጣብ ሲቆርጡ በሥፍራው የነበረው ሕዝብ ወደ ልማት የሚደረገውን ጉዞ የሚመሩትን መሪ በማየቱ ደስታውን በጭፈራ ገልጿል'' ሲል ነበር ጣቢያው በዜና ያወጀው።

ኪም፤ በፋብሪካው እንቅስቃሴ መደሰታቸውንና በአገሪቱ እየታየ ላለው የኬሚካል ኢንዱስትሪና ምግብ ምርት ዕድገት አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለው እንደሚያምኑም ጣቢያው ዘግቧል።

ኪም ሞተዋል የሚል ጥርጣሬ ከየት መጣ?

ኪም ሞተዋል አልያም ጤናቸው ተቃውሷል የሚል ጥርጣሬ የመጣው ሰሜን ኮሪያን የመሠረቱት አያታቸው ኪም ሱንግ ሁለተኛ የልደት በዓል ላይ ባለመታየታቸው ነው።

ዓመታዊው ክብረ-በዓል ሰሜን ኮሪያ ውስጥ በትልቁ የሚከበርና መሪው ኪምም ቀርተውበት የማያውቅ ቀን ነው።

ከሰሜን ኮሪያ ባመለጡ ሰዎች የሚተዳደር አንድ ድረ-ገፅ የኪም ጤና ሳይቃወስ አልቀረም ብሎ ማስነበቡ ደግሞ ጥርጣሬውን የጎላ አደረገው። አልፎም ዴይሊ ኤንኬ ለተባለው ጋዜጣ አንድ ታማኝ የተባለ ምንጭ ኪም ከልብ ጋር የተገናኘ ሕመም አለባቸው ብሎ ተናገረ።

የፎቶው ባለመብት, AFP

እነዚህ ዜናዎች ተደማምረው ኪም በጠና ታመው አሊያም ሞተዋል የሚሉ ዜናዎች መነበብ ጀመሩ። ይህንን ተከትሎም የአሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ስለላ ሠራተኞች ወሬውን ማጣራት ያዙ።

ከዚህ በኋላ ነው የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ኪም በጠና ታመዋል እያሉ መዘገብ የጀመሩት። የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፓምፔዮ ኪምን በቅርብ አይቻቸው አላውቅም ማለታቸው ወሬውን አጦዘው።

ነገር ግን ከደቡብ ኮሪያና ቻይና የስለላ ምንጮች የወጡ መረጃዎች ወሬው ሐሰት ነው ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

ኪም ጆንግ ኡን ከዚህ በፊትም የዛሬ 6 ዓመት ለ40 ቀናት ከሚድያ ጠፍተው ብዙ ተወርቶ ነበር። የደቡብ ኮሪያ ስለላ ድርጅት ግራ እግራቸው ላይ ቀዶ ጥገና ሳያደርጉ አልቀረም ቢልም ማጣራት ግን አልተቻለም።