ትዊተር ላይ በፃፈው ምክንያት የኩባንያውን 14 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያጣው ኢላን መስክ

ኢላን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ከትዊቶቹ ብዙዎችን ያስደነቀው ማንኛውም ዓይነት ንብረት እንዲኖረኝ አልሻም። ቤት ንብረቴን ልሸጥ ነው ብሎ 'የተወተው' ነው

የቴስላ መሥራች የሆነው ኢላን መስክ ትዊተር ላይ በፃፈው ምክንያት የኩባንያውን የአክስዮን ገበያ 14 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ማጣቱ ተነገረ።

አልፎም ከእራሱ አክስዮን ዋጋ 3 ቢሊየን ዶላር ማጣቱም ተዘግቧል። ይህ የሆነው ኢንቨስተሮች የገዙትን አክስዮን እየያዙ በመውጣታቸው ምክንያት ነው።

"በእኔ እይታ የቴስላ አክስዮን ድርሻ ጣራ ነክቷል" ሲል በትዊተር ሰሌዳው ላይ የፃፈው ኢላን ሰዎች ጤነኝነቱን እንዲጠራጠሩ አድርጓል።

ቀጥሎ በሰሌዳው ላይ ባሰፈረው ባለሁለት አረፍተ-ነገር ፅሁፍ ደግሞ ያሉት ንብረቶች ሁሉ እንደሚሸጥ አስታውቋል።

ከዚያም በማስከተል ባሠፈረው መልዕክት ደግሞ የፍቅር ጓደኛው በሆነው ሁኔታ እንደተናደደችበት አሳውቋል። ከዚያ ሻገር ብሎም "የንቃተ-ኅሊና ብርሃን እየጠፋ ነውና በቁጣ እንነሳ" የሚል ዓይነት መልዕክት ያለው ፅሑፍ በትዊተሩ ገፁ ታይቷል።

ግለሰቡ ለመሰል ግራ አጋቢ 'ትዊቶች' አዲስ አይደለም። ከሁለት ዓመት በፊት ቴስላ የኒው ዮርክ አክስዮን ገበያ ላይ ስላለው ድርሻ የፃፈው ፅሑፍ 20 ሚሊዮን ዶላር እንዲቀጣ አድርጎታል።

ዎል ስትሪት ጆርናል ቢሊየነሩን ስለ አክስዮን ድርሻ ትዊተር ላይ ያሰፈርከው ነገር ቀልድ ነው? ሌላስ ሰው አስተያየት ሰጥቶበታል? ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ 'አይደለም' የሚል አጭር ምላሽ አግኝቷል።

በኤሌክትሪክ የሚሠራው ቴስላ መኪና ኩባንያ የአክስዮን ገበያ በዚህ ዓመት ተመንጥቆ ነበር። የኩባንያው የአክስዮን ድርሻም 100 ቢሊየን ዶላር ደርሷል። ይህ ማለት ቢሊየነሩ መቶ ሚሊዮን ዶላሮች እንደ ጉርሻ ያገኛል ማለት ነው።

ለሮይተርስ ዜና ወኪል ሃሳባቸውን የሰጡ አንድ የአክስዮን ገበያ ባለሙያ የሰውየው 'ትዊቶች' ለኢንቨስተሮች ራስ ምታት ናቸው ይላሉ።

መስክ ከሁለት ዓመት በፊት ቴስላን ለብቻው ማስተዳደር የሚያስችለው ገንዘብ ስላገኘ ከአክስዮን ገበያው ሊያስወግደው እንደሚችል ፅፎ እንዲሁ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች ዋጋ ማጣቱ አይዘነጋም። ግሰለቡ በመሰል ትዊቶቹ በሕግ ሊቀጣ እንደሚችልም እየተዘገበ ነው።

ትዊተር ላይ 33.5 ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት መስክ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ቤታቸው እንዲቀመጡ መደረጋቸው ተገቢ አይደለም ብሎም ፅፎ ነበር።

ከትዊቶቹ ብዙዎችን ያስደነቀው ማንኛውም ዓይነት ንብረት እንዲኖረኝ አልሻም። ቤት ንብረቴን ልሸጥ ነው ብሎ የጻፈው ነው።