ኮሮናቫይረስን ለማከም ስለተፈቀደው መድኃኒት ሬምዴሲቬር ምን ይታወቃል?

የኮሮናቫይረስ ህሙማንን ለማከም እንዲውል የተፈቀደው ሬምዴሲቬር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የኮሮናቫይረስ ህሙማንን ለማከም እንዲውል የተፈቀደው ሬምዴሲቬር

የአሜሪካ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር ተቋም ለኢቦላ በሽታ የሚውለውን ሬምዴሲቬር የተባለውን መድኃኒት ለአስቸኳይ ጊዜ የኮሮናቫይረስ ህክምና እንዲውል ፈቀደ።

በዚህም መሰረት ይህ ጸረ ቫይረስ የሆነው መድኃኒት በኮሮናቫይረስ በጽኑ ታመው ሆስፒታል የሚገኙ ሰዎችን ለማከም ይውላል።

የአሜሪካ ምግብና መድኃኒት አስተዳደር ኮሚሽነር የሆኑት ስቴፈን ሃን "ይህ የኮሮናቫይረስን ለማከም ዕውቅና የተሰጠው የመጀመሪያው መድኃኒት ነው" ብለዋል።

በቅርቡ ሬምዴሲቬርን በመጠቀም በተደረገ ሙከራ በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ታመው ሆስፒታል የገቡ ሰዎች የሚያገግሙበትን ጊዜ ማፋጠን እንዳስቻለ ተረጋግጧል።

ነገር ግን ይህ በተቋሙ መድኃኒቱን ለመጠቀም የተሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ ፈቃድ ሙሉ ፈቃድ አለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ መደበኛ ዕውቅና ለማግኘት ከፍ ያለ ምዘናን ይጠይቃል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ይህ ኢቦላን ለማከም የተሰራው መድኃኒት ኮሮናቫይረስን እንደሚፈውስ ተአምረኛ መፍትሄ መወሰድ የለበትም።

ስለሬምዴሲቬር የምናውቀው

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህ ሬምዴሲቬር የተባለው የኢቦላ መድኃኒት የኮሮናቫይረስን ለማከም ጥቅም ላይ እንዲውል ከፍተኛ ድጋፍ ሲሰጡ ቆይተዋል።

ሬምዴሲቬር ሰዎች ከኮሮናቫይረስ በፍጥነት እንዲያገግሙ እንደሚረዳ በአሜሪካ የጤና ባለስልጣናት ዘንድ ጠንካራ እምነት ተጥሎበታል።

በተጨማሪም መድኃኒቱ የህሙማኑን ህይወት በመታደግ በኩልም አቅም እንደሚኖረው የታመነ ሲሆን፤ መድኃኒቱን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል ከተቻለ በሆስፒታሎች ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ ያስችላል። በተጨማሪም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫናን ያስከተለውን የእንቅስቃሴ ገደብ በተወሰነ ደረጃ ለማላላት ሊያግዝ ይችላል ተብሏል።

ኢቦላን ለማከም የተሰራው ሬምዴሲቬር የጸረ ቫይረስ መድኃኒት ሲሆን፤ በዋናነት ኢላማ የሚያደርገው በህዋሳት ውስጥ ቫይረስ እንዲባዛ የሚያግዘውን ኤንዛይም በማጥቃት ማስቆም ነው።

የአሜሪካ ብሔራዊ የአለርጂና ተላላፊ በሽታዎች ምርምር ተቋም በሬምዴሲቬር ላይ ባደረገው የሙከራ ምርምር መድኃኒቱ በኮሮናቫይረስ ህሙምን ላይ የሚታየውን የበሽታውን ምልክቶች ቆይታ ከ15 ቀን ወደ አስራ አንድ ዝቅ ማድረጉን አመልክቷል።

ሙከራው በዓለም ዙሪያ ያሉ ሆስፒታሎችን በማካተት በ1,063 ሰዎች ላይ የተካሄደ ሲሆን፤ ለተወሰኑት መድኃኒቱን የተሰጣቸው ሲሆን ለሌሎቹ ደግሞ ምንም ውጤት የማያመጣ ማስመሰያ መድኃኒት ተሰጥቷቸው ነበር።

የተቋሙ ኃላፊና የፕሬዝዳንቱ የጤና አማካሪ የሆኑት ዶክትር አንቶኒ ፋውቺ በሙከራው ስለተገኘው ውጤት "ሬምዴሲቬር የኮሮናቫይረስ ህሙማን የሚያገግሙበትን ጊዜ በማሳጠር አዎንታዊ፣ ግልጽና ከፍ ያለ "ውጤትን እንዳሳየ አመልክተዋል።

ነገር ግን ሬምዴሲቬር በኮሮናቫይረስ የታመሙ ሰዎች በቶሎ እንዲያገግሙ ምናልባትም ክፉኛ ታመው ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል እንዳይገቡ ሊያደርግ ቢችልም በሽታውን ሙሉ በሙሉ በመፈወስ በኩል የተረጋገጠ ነገር የለም።

በተጨማሪም በመድኃኒቱ ላይ የተደረጉት ሙከራዎች ሬምዴሲቬር በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ ሞቶችን በማስቀረት በኩል ያለውን ጠቀሜታ የሚያመለክት ግልጽ የሆነ ውጤት አልታየም።

ይህ ሬምዴሲቬር የተባለው መድኃኒት የተፈጠረውና የዳበረው 'ጊሌድ ሳይንስስ' በተባለው ተቋም ኢቦላንና ማርበርግ የተባሉትን በቫይረስ የሚመጡ በሽታዎችን ለማከም በተደረገ ጥናት አማካይነት ነው።

በኋላ ላይም ይህ መድኃኒት በተለያዩ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎችና በሌሎችም በቫይረስ በሚመጡ በሽታዎች ላይ የጸረ ተህዋስነት ባህሪይ እንዳለው ጊሌድ ሳይንስስ ደርሶበታል።

በጥቅምት ወር 2015 (እአአ) የአሜሪካ ጦር ሠራዊት የተላላፊ በሽታዎች ህክምና ምርምራ ተቋም በዝንጀሮዎች ላይ ባደረገው ሙከራ ሬምዴሲቬር የኢቦላ ቫይረስን ማገድ እንደሚችል አስታወቋል።

ከዚያም ከ2013-2016 ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ በምዕራብ አፍሪካ አገራት ውስጥ ባጋጠመው የኢቦላ ወረርሽኝ ሰብብ በፍጥነት በሰዎች ላይ እንዲሞከር ከተደረገ በኋላ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለማከም ጥቅም ላይ ውላል።