ኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ የዘረ-መል ለውጥ የተደረገባቸው የእህል ዘሮችን ለማምረትና ለመጠቀም አልተስማማችም

የግብርና ሰራተኞች ችግኞችን ሲንከባከቡ

የፎቶው ባለመብት, UniversalImagesGroup

ኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ የዘረ-መል ለውጥ የተደረገባጋቸው ሕያዋን (ጄኒቲካሊ ሞዲፋይድ ኦርጋኒዝም) የእህል ዘሮችን ለማምረትም ሆነ ለመጠቀም እንዳልተማማች ተገለጸ።

የግብርና ሚኒስቴር ለቢቢሲ፤ ሰሞኑን ኢትዮጵያ ልውጥ ሕያዋንን ለማምረትና ለመጠቀም በሯን ለመክፈት ተስማምታለች በሚል የሚነገረው ትክክል እንዳልሆነ ገልጿል።

ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ ኢትዮጵያ ልውጥ ሕያውን (ጀኒቲካሊ ሞዲፋይድ ኦርጋኒዝምስ፤ ጂኤምኦ) በሚመለከት ከእራሷ ባሻገር ሌሎች አገራትም የሚከተሉት ጠንከር ያለ አቋሟን አለዝባ እንደተቀበለች ሲዘገብ እና በጉዳዩም ላይ ሚናዎች ተለይተው ክርክሮች ሲደረጉ ተስተውሏል።

በወርሃ የካቲት የአሜሪካ መንግሥት የግብርና መስሪያ ቤት የውጭ አገራት ግብርና አገልግሎት እና በዓለም አቀፉ የግብርና መረጃ መረብ የታተመ የግብርና ሥነ- ሕይወት ቴክኖሎጂ ግምገማ የኢትዮጵያ መንግሥት በግብርና ሥነ ሕይወት ዘርፍ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ፍላጎት በግልፅ ማሳየቱን አመልክቶ ነበር።

የአሜሪካ የግብርና መስሪያ ቤት ሠራተኞችን ግምገማ ቢያካትትም የአገሪቱን አቋም ግን አይገልፅም በተባለው በዚህ ዘገባ ላይ እ.ኤ.አ በ2018 የኢትዮጵያ መንግሥት የሥነ ሕይወት ለውጥ የተደረገለትን የጥጥ ዝርያ (ቢቲ-ኮተን) መቀበሏን፤ ድርቅን እና ፀረ ሰብል ተባይን የሚቋቋም የበቆሎ ዝርያ ላይም በቦታ የተከለለ የመስክ ላይ ጥናት እንዲደረግ መፍቀዷን ጠቅሷል።

ስለጉዳዩ ለማጣራት ቢቢሲ ያነጋገራቸው በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ምርት ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ "ኢትዮጵያ በሰፋፊ እርሻዎች በባለሃብቶች ብቻ ለማምረት ሁለት ጂኤምኦ የጥጥ ዝርያዎችን ብትመዘግብም፤ ይህ በጥቅሉ አገሪቱ እነዚህን ምርቶች ተቀብላለች ወደሚል ድምዳሜ መድረስ አይቻልም" ይላሉ።

"ሁለት ዝርያዎችን ከህንድ አምጥተን ሞክረን፤ ስኬታማ ናቸው ተብሎ በዝርያ ደረጃ ተመዝግበዋል። ሌሎች አገራት እንደሚያደርጉት ለእህል ግን አልፈቀድንም" ብለዋል አቶ ኢሳያስ።

እ.ኤ.አ በ2018 የተመዘገቡት ሁለት ሰው ሰራሽ የዘረ መል ለውጥ የተደረገባቸው የጥጥ (ቢቲ-ኮተን) ዝርያዎች ተቀባይነት አግኝተው ምዝገባ ይደረግላቸው እንጂ ወደሥራ ለመግባት ገና የሚቀሩ ደረጃዎች እንዳሉ አቶ ኢሳያስ ጨምረው ገልፀዋል።

እነዚህ ዝርያዎች ጥጥን በሚያጠቃ አንድ ተባይ ምክንያት የተሻለ የመቋቋም አቅም ካላቸው ተብሎ እንደተሞከረና ምርምሩ አብቅቶ የተባሉት ዝርያዎቹ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

"ቀጥሎ ያለው ዘሩ እንዴት ነው በታጠረ፥ ማለትም በባለሃብት ብቻ እንዲለማ የሚደረገው ወደሚለው ቀጣይ እርምጃ ለመሄድ ዘር መግባት ነበረበት። ይሄን የዘር ሒደት ተስማምተን አልጨረስንም፤ ገና ነው። ዘር አልገባም፣ ዝርያዎቹ እንዴት ይሰራሉ የሚለው መመርያም አልፀደቀም" ይላሉ።

ዝርያዎቹን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እንቅፋት ከሆኑ ጉዳዮቹ አንዱ ዝርያዎቹን የሚያመርተው የህንድ ኩባንያ የብቸኛ አቅራቢነት (ሞኖፖሊ) አሠራር ያለው መሆኑን ዳይሬክተሩ ለቢቢሲ ተናገረዋል።

በሰፋፊ እርሻዎች ለንግድ አገልግሎት ብቻ ይውላሉ የተባሉት እነዚህን ዝርያዎች ሥራ ላይ ከማዋል ጋር በተገናኘ፥ "ከሕንዱ ኩባንያ ጋር መስማማት አለብን፤ አንደኛ ዝርያዎቹ እዚህ መባዛት አለባቸው። ዝርያዎቹ ከተመዘገቡ በኋላ እኔ ዘሩን በየዓመቱ አቀርባለሁ ከሚለው [የኩባንያው ሐሳብ] ጋር አልተስማማንም። ከሌላው የጥጥ ዝርያ ጋር እንዳይቀላቀል የማድረጉን ሒደትም ገና አልተሄደበትም። በዚያ ላይ ተንጠልጥሎ ነው የቀረው።"

ኢትዮጵያ በ2001 ዓ.ም ያፀደቀችው የደኅንነተ ሕይወት አዋጅ ሰው ሰራሽ የዘረ መል ለውጥ የሚደረግባቸው ሕያዋን ላይ የሚደረጉ ምርምሮች ላይ በሮችን ጠበብ ያደረገ ነበር።

አዋጁን ሆን ብሎ ጂኤምኦን ወደ ከባቢ መልቀቅን ይከለክላል በሚል በዘረ መል ብዝሃነት የዳበረ ከባቢዋን ከዝርያ መበከል ለመታደግ ችላለች በሚል ያሞካሿት ነበሩ።

ይሁንና ከስድስት ዓመታት በኋላ በአዋጁ ላይ ማሻሻያዎችን አድርጋ በሩን ሰፋ አድርጋለች እየተባለ ነው።

አዋጆቹ በሚፀድቁባቸው ጊዜያትም ቢሆን በጂኤምኦ ዝርያዎች ዙርያ ጥቅም እና ጉዳት እየዘረዘሩ ሐሳባዊ ሙግቶችን ያደረጉ የዘርፉ ባለሞያዎች ነበሩ።

እነዚህ ሙግቶች አሁንም ሲያስነሰራሩ እየተስተዋለ ነው።

ጂኤምኦን የሚቃወሙ ወገኖች ሰው ሰራሽ የዘረ መል ለውጥ የሚደረግባቸው ዝርያዎች ቀድሞ ያልታሰበ ጉዳት ሊያመጡ ይችላሉ፤ ከዚህም በዘለለ ዝርያዎቹ ላይ ምርምር የሚያደርጉ ትልልቅ የግል ኩባያዎች የባለቤትነት መብት ስለሚኖራቸው፥ ገበሬዎች የእነርሱ ጥገኞች እንዲሆኑ ያደርጋሉ ይላሉ።

በሌላ በኩል የጂኤምኦ ዝርያዎች ከትንሽ መሬት ብዙ ምርትን ያሳፍሳለሉ፥ ለተፈጥሯዊ ጫናዎች እና ጉዳት አማጭ ተባዮች በቀላሉ አይበገሩም ሲሉ ያሞግሷቸዋል ደጋፊዎቻቸው።