ኮሮናቫይረስ፡ “ያልተፈተነ መድኃኒት አትውሰዱ” የአለም ጤና ድርጅት

የማዳጋስካር ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአለም ጤና ድርጅት ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጡ መድኃኒቶችን ለኮሮናቫይረስ በማለት ሰዎች እንዳይወስዱ አስጠነቀቀ።

ምንም እንኳን በአፍሪካ ውስጥ ለኮሮናቫይረስ ፈውስ ተብለው የቀረቡት ከአገር በቀል የተቀመሙ መድኃኒቶች ቢሆኑም እንኳን፤ ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መድኃኒቶች መሆን አለባቸው። አፍሪካውያንም ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ መድኃኒቶች አቅርቦትን የማግኘት መብት አላቸው ተብሏል።

የማዳጋስካሩ ፕሬዚዳንት ከዕፅዋት የተቀመመ የኮቪድ19 መድኃኒት ተገኝቷል በማለትም እያስተዋወቁ ባለበት ወቅት ነው ይህ መግለጫ የወጣው።

የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ መድኃኒቱ “ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑና አዳኝነቱን” በተመለከተ ሳይንሳዊ ድጋፎችን እንዲቀርቡለት ጠይቋል።

ከተለያዩ እፅዋት የተቀመመው መድኃኒት በባለፉት ሶስት ሳምንታት በሃያ ሰዎች ላይ ሙከራ መደረጉን የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይህም የአለም አቀፉ ጤና ድርጅት ካወጣው መመሪያ ጋር ይጣረሳል ተብሏል።

መድኃኒትም ለማግኘት ረዘም ያለ ጊዜና የተለያዩ ደረጃዎችንም ማለፍ እንዳለበት ተጠቁሟል። ህዝቡ መድኃኒቱን እንዲወስደው ከመደረጉም በፊት በጥቂት ሰዎች ላይ ተሞክሮ ፈዋሽነቱ መረጋገጥ ይኖርበታል።

ይሁን እንጂ ጊኒ ቢሳው፣ ኢኳቶሪያል ጊኒና ላይቤሪያ ከዕፅዋት የተቀመመውን መድኃኒት ወደ ሃገራቸው እንዲመጣ አዘዋል። መድኃኒቱ የተሰራው የወባ በሽታንና ለሌሎችም በሽታዎች መድኃኒት ከሆነው የአሪቲ ቅጠል (አርቲሚዥያ)ና ሌሎችም ዕፅዋት መሆኑ ተነግሯል።

ባለፈው ሳምንት የማዳጋስካር ፕሬዚዳንት አንድሬ ራጆይሊና ስለ መድኃኒቱም ለማስረዳት ከተለያዩ አፍሪካ መሪዎች ጋር በ’አንላይን’ ስብሰባቸውን አድርገዋል።

ከስብሰባውም በኋላ የአፍሪካ ህብረት ስለ መድኃኒቱ ዝርዝር የጠየቀ ሲሆን ይህም በአፍሪካ የበሽታዎች ቁጥጥርና ክትትል ማዕከል ግምገማ የሚደረግበት ይሆናል።

የአለም አቀፉ ጤና ድርጅት እንዲህ አይነት አገር በቀል መድኃኒቶችን ለመድኃኒትነት የማዋል ግኝት “ይበል የሚያሰኝ ነው” ካለ በኋላ ሆኖም “ የጎንዮሽ ጉዳትና አዳኝነቱን” በተመለከተ ምርመራ ያስፈልጋል ብሏል።

“አፍሪካውያን እንደተቀረው አለም ደረጃውን የጠበቀ መድኃኒት መውሰድ ይገባቸዋል” ብሏል በመግለጫው

ለኮሮናቫይረስ የክትባት ሙከራ፣ ምርምር ስራዎች፣ እንዲሁም መድኃኒት ለማግኘትና ለእንክብካቤ ስምንት ቢሊዮን ዶላር በዚሁ ሳምንት ተመድቧል።

በአለም ላይ የተጀመሩ የክትባት ሙከራዎችም ቁጥር በርካታ ነው።

ሆኖም በርካታ በዘርፉ ላይ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ክትባቱ እስከ ጎርጎሳውያኑ 2021 አጋማሽ ድረስ ሊቆይ እንደሚችል ይናገራሉ።

የኮሮናቫይረስ በተከሰተ ማግስት የቤት መቀመጥ እንዲሁም የሰአት እላፊ አዋጆችን አስተላልፈው የነበሩ ሃገራት ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ጋር ለማጣጣም ህጎቻቸውን አላልተዋል። ህጎቹን ማላቱን ተከትሎ የመድኃኒቱን ፍለጋ ጥያቄዎችም በርትተዋል።

በማዳጋስካር 151 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ሞት አልተከሰተም።

ፕሬዚዳንቱ በትላልቅ ሶስት ከተሞች ጥለዋቸው የነበሩ የቤት መቀመጥ አዋጆችን ማላላታቸውንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።