“'ሥልጣንን ያለ ምርጫ ካልሰጣችሁኝ አገር አተራምሳለሁ' በሚል ኃይል ላይ እርምጃ እንወስዳለን” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

የፎቶው ባለመብት, PM office

ስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ በኮቪድ-19 ስጋት ከመራዘሙ ጋር ተያይዘው በሚሰጡ አማራጭ ኃሳቦች ላይ የሽግግር መንግሥት እንመሰርታለን የሚለው አስተያየት ህገ መንግሥታዊ መሰረት የሌለውና በዚህ ወቅት መነሳቱም ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ህገ - መንግሥቱ ከደነገገው ውጭ ያለ ምርጫ እንዲሁም በህገ ወጥ ምርጫ ስልጣን እቆናጠጣለሁ ብሎ የሚያስብ አካል የሃገሪቱንም ብቻ ሳይሆን አለም አቀፍ ድንጋጌዎችን እንደሚጥስ ከመጠቆም በተጨማሪ መንግሥታቸው እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀዋል።

“ ከህግ አግባብ ውጭ ስልጣን ካልሰጣችሁኝ አገር አተራምሳለሁ የሚለውን ማንኛውንም ኃይል አንታገስም፤ በቂ ዝግጅትም አለን።” ብለዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ዋነኛ ኃላፊነት ህገ መንግሥቱን የመጠበቅና የመከላከል ዋነኛ ኃላፊነት መሆኑንም ገልፀው፤ ይህንን ተግባራዊ በማያደርጉና "የጨረባ" ምርጫ ለማድረግ እንነሳለን በሚሉም ወሳኝ እርምጃ ለመውሰድ መንግስታቸው እንደሚገደደም በአፅንኦት ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት መሰረት መንግሥት ለመመስረት ምርጫ ግዴታ እንደሆነ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫ ሳይካሄድ ስልጣን ላይ መውጣት ህጋዊ መሰረትም የለውም ብለዋል።

“የፖለቲካ ፓርቲ ስለሆንኩ ስልጣን ይገባኛል የሚለው ፈሊጥ ዲሞክራሲያዊም ሆነ ህገ መንግሥታዊ አካሄድ አይደለም፤ ያለ ምርጫ እንዲሁ ተጠራርቶ ስልጣን የሚከፋፈልበት ሁኔታም አያስሄድም" ብለዋል።

በተለያዩ ሃገራት ውስጥ የተመሰረቱ የሽግግር መንግሥታት እንዴት ተመሰረቱ? የሚለውን ልምድ ያካፈሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአብዛኛውም ከወታደራዊ ወደ ዲሞክራሲያዊ በሚደረግ ሽግግርና ህገ መንግሥትም እስኪፀድቅ ድረስ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እውነታ ለውጥ እንጂ አብዮት ባለመሆኑ የሽግግር መንግሥት ተቀባይነት የሌለው ኃሳብ ነው ብለዋል።

“የኮቪድ- 19 ስጋት ባለበትና የቀጠናው ሁኔታው የሃገሪቱን ሉዓላዊነት በሚፈታተንበት ወቅት የሽግግር መንግሥት እመሰርታለሁ ማለት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው፤ ህገ ወጥም ብቻ ሳይሆን አደገኛ ነው” በማለት ተናግረዋል።

ከመቶ በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራድረው በሚያመጡት ፖለቲካዊ መፍትሄ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ማለት ሃገሪቷ እየገነባች ያለቸውንም ዲሞክራሲያዊ ስርአት ወደኋላ የሚመልስ ነው በማለት አፅንኦት ሰጥተዋል።

“ህግ በጣሰ ሁኔታ ስልጣን እንደ ድግስ ትሩፋት ይዳረስ የሚለው አካሄድ ትክክል አይደለም፤ ለመሆኑ የተመረጠ መንግሥት እያለ ያልተመረጡ ፓርቲዎች ተሰባስበው መንግሥት የሚመሰርቱት በየትኛው የሞራል፣ የህግና የስርአት አካሄድ ነው” በማለት ይጠይቃሉ።

አክለውም “ለወራት ምርጫን ማራዘም ወይስ? ለአመታት ለሽግግር መንግሥት ብሎ የብጥብጥና የሁከት መንግሥት መፍጠር ነው ኢትዮጵያን ለአደጋ የሚያጋርጣት?” ሲሉም ጠይቀዋል።

በነሐሴ ወር ለማካሄድ ታቅዶ የነበረውን ምርጫ በኮቪድ-19 ምክንያት ከመራዘሙ ጋር ተያይዞ በርካታ ጥያቄዎችም መነሳት ጀምረዋል።

ከሰሞኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሁን ባለው የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ምርጫውን ማካሄድ አስቸጋሪ በመሆኑ የምርጫ ጊዜንም በማራዘም ምርጫው ከሚካሄድበት አራት አማራጮች መካከል ‘ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ መጠየቅ’ የሚለውን አማራጭ አፅድቋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ህገ መንግሥታዊ ትርጓሚ እንዲሰጥበትና ለህገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ መርቶታል።

መንግሥት ያቀረባቸውም አራት አማራጮች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መበተን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ ሕገ መንግሥትን ማሻሻልና የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚሉ ናቸው።

መንግሥትም የተለያዩ አማራጮችን በህግ ባለሙያዎች ሲያስጠና እንደነበር የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሃገሪቱንም ሆነ የተለያዩ የህግ ድንጋጌዎችን በማስገባት አማራጭ ያሏቸውን ህጋዊ አግባብ በተመለከተ ያቀረቡ ሲሆን ከባለድርሻ አካላትም ጋር ውይይት ተደርጓል።

በህግ አውጭው የሚቀርብ የህገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ በብዙ ሃገራት የተለመደና ህገ መንግሥታዊ ሃሳቦችን ወደ መሬት ማውረጃ መንገድ እንደሆነም በዛሬው ዕለት ተናግረዋል።

ከህዝቡም ይሁን ከተለያዩ አካላት የተለያዩ አማራጮች እየቀረቡ እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህግ ባለሙያዎች ምርጫን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማራዘም እንደሚቻልና የተሻለው አማራጭ ይህ እንደሆነ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

በዚህ መልክ ምርጫው በመተላለፉ በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት እስከ ቀጣዩ ምርጫ በስራ ላይ የሚቀጥል እንደሆነ እነዚሁ የህግ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን እንደሰጡም ጠቁመዋል።

“መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብቻውን ብዙ ርቀት መሄድ እየቻለ ወይም በቀላሉ ህገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ማድረግ እየቻለ ጉዳዩን ለምክክርና ለውይይት ማቅረቡ አሳታፊ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት በግልፅ ያሳያል” ብለዋል።

ከበርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራትም ጋር በተደረጉ ውይይቶች ህገ መንግሥታዊ ትርጓሜ የተሻለ አማራጭ መሆኑንም ለማረዳት እንደቻሉ ገልፀዋል።

“ይህ አማራጭ የተሻለ ነው የተባለው ዛሬ የገጠመንን ፈተና በማየት ብቻ አይደለም ለወደፊቱም ህገ መንግሥታዊነትን በሃገራችን እንዴት እናጎልብት እንችላለን የሚለውንም በማሰብ ጭምር ነው። ይህ አጋጣሚ እኛም ህገ መንግሥታችንን በትርጓሜ የምናዳብርበት አዲስ ምዕራፍ ይከፍትልናል ” ብለዋል

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካናዳ፣ ጀርመን፣ ህንድ፣ አሜሪካና የመሳሰሉ ሃገራት ግንባር ቀደም ህገ መንግሥታዊ ስርአት ተደርገውም የተቆጠሩት በህገ መንግሥት ትርጓሜ ህገ መንግሥቶቻቸውን ያሉባቸውን ክፍተቶች በመሙላት ነው ካሉም በኋላ ኢትዮጵያ ከዚህ ትምህርት መቅሰም እንደሚገባት አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ “ሃገሪቷ የገጠማት ህገ መንግሥታዊ ቀውስ ነው፤ ህገ መንግሥቱ ለዚህ ችግር ምንም አይነት ምላሽ፤ ምርጫን የሚያራዝም መንገድ በህገ መንግሥቱ አልተጠቀሰም’ “”ለህገ መንግሥቱ ትርጓሜን መነሻ የሚሆንና ይህንን ጉዳይ የተመለከተ ህገ መንግሥታዊ አንቀፅ የለም” የሚሉ መከራከሪያ ሃሳቦች በተደጋጋሚ ይሰማሉ።

ከዚህም ጋርም ተያይዞ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የህግ ባለሙያዎች አማራጮቹ የተወሰኑ ቢሆንም አሉ እያሉ ጥናት ያላዳረጉ አካላት፤ ህጋዊ መፍትሄ የሌለው ችግር ነው ማለታቸው ምኞታቸውን እንጂ እውነታውን አያሳይም” በማለት ተናግረዋል

አክለውም “ህጋዊ መፍትሄ የለም ማለታቸው ህጋዊ መፍትሄ አንፈልግም ማለታቸው ነው፤ ህጉ በአቋራጭ ስልጣን እንድንቆናጠጥ አያደርገንም ማለታቸው ነው”

ህገ መንግሥቱ በቀጥታ ባይላቸውም በህገ መንግሥቱ ትርጓሜ የሚመለሱ ጥያቄዎች፤ በተለያዩ አገራትም በትርጓሜ ለወሳኝ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት እንደተቻለ ገልፀው ትርጓሜ ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም ለሚለው ጥያቄን መመለስ ያለበት ስልጣን የተሰጠው ለገለልተኛ የህገ መንግሥቱ አጣሪ ጉባኤ ሊመልስ ይገባል።

“ጉባኤው ወደ ፍርድ ቤትነት የተጠጋ ህገ መንግሥታዊ ተቋም ነው።የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚመራውም በብልፅግና ፓርቲ አይደለም። የትርጓሜው ሂደት በአንድ ፓርቲ ስር ነው ያለ ለማለት አይቻልም” ብለዋል

የትርጓሜውንም የሃሳብ ውሳኔ የሚያቀርቡ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና በምክትል የሚመራ ገለልተኛ አካል ነው።

“ሁሉም ህገ መንግሥቱን ተርጓሚና የህገ መንግሥት ዳኛ እሆናለሁ ካለ ለዲሞክራሲና ለህገ መንግሥታዊነት የማይበጅ ምስቅልቅል አካሄድ ነው” ብለዋል

በህገ መንግሥቱ መሰረት የፓርላማ አባላት የስልጣን ጊዜ ማብቂያ በመጪው መስከረም እንደሆነ ጠቅሰው ከዚያ በኋላ ግን ተቀባይነት የሌለው፣ ህጋዊ መሰረት የሌለውና አለም አቀፍ እውቅናም የማይኖረው መንግሥት ይሆናል የሚል መከራከሪያዎች በተለያዩ አካላት እየቀረቡ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ

" አሁን ያለው መንግሥት ህግ የሚያወጣ፣ አለም አቀፍ ድንጋጌዎችን የሚቀበል፣ በጀት የሚያፀድቅ መንግሥት ነው፤ ህጋዊ በሆነ አግባብ የኮቪድ-19 ስጋት እስኪወገድና ቀጣይ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ሃገር መምራት ኃላፊነት ያለበት ፓርቲ ነው” ብለዋል።