ኬንያ ሶማሊያ እና ሩዋንዳ በከባድ ጎርፍ ተመቱ

በጎርፍ የተጠቁ ነዋሪዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

በምስራቅ አፍሪካ በጣለ ከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተ ጎርፍ ከ 260 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል።

በጎርፉ ክፉኛ የተጎዳችው ኬንያ ስትሆን 194 ሰዎች ሕይወታቸን ማጣታቸው ታውቋል።

በሩዋንዳ ደግሞ በዚሁ ጎርፍ ምክንያት 55 ሰዎች የሞቱ ሲሆን በሶማሊያ 16 ሰዎች ሞተዋል። በኡጋንዳ ጎርፉ ባስከተለው መጥለቅለቅ 200 የሚሆኑ ታካሚዎች ከአንድ ሆስፒታል ውስጥ መውጣት አቅቷቸው እስካሁን እዛው መሆናቸው ተዘግቧል።

የምስራቅ አፍሪካ አገራት በአሁኑ ሰአት የኮቪድ-19፣ የአንበጣ መንጋ እና የጎርፍ አደጋ እየፈተኗቸው ነው።

ይህ ጎርፍ እስካሁን ከ3000 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የነበረ ሰብልም ሙሉ በሙሉ አጥፍቷል። የአየር ትንበያ ባለሙያዎች እንደሚሉት ዝናቡ ከዚህም በላይ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይችላል።

በሩዋንዳ ከጎርፉ በተጨማሪ በርካቶች በመሬት መንሸራተት ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን መኖሪያ ቤቶች፣ ዋና ዋና መንገዶችና የእርሻ ማሳዎች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።

በምዕራባዊ ዩጋንዳ ደግሞ አንድ ወንዝ ሞልቶ ወደ ውጪ በመፍሰሱ በርካቶች ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ተሰደዋል። በዚህም ምክንያት ቤት አልባ የሆኑ ሰዎች መንግስት ድረስልን እያሉ ይገኛሉ።

በቅርብ ሳምንታት በአፍሪካ ትልቁ የሆነው ቪክቶሪያ ሐይቅ ከሚገባው በላይ በመሙላቱ በዙሪያ የነበሩ ነዋሪዎች ቤታቸውን ትተው ሸሽተዋል። ከባድ የአፈር መሸርሸርም አስከትሏል።