ኮሮናቫይረስ፡ ባራክ ኦባማ አሜሪካ ለወረርሽኙ የሰጠችውን ምላሽ "ቅጥ አምባሩ የጠፋው" ሲሉ ተቹ

የቀድሞው አሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ባራክ ኦባማ ከጎርጎሳውያኑ 2009 እስከ 2017 ድረስ አሜሪካን በፕሬዚደንትነት አስተዳድረዋል

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ቀውስ ለመቆጣጠር በሰጡት ምላሽ ላይ ተተኪያቸውን ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕን በከፍተኛ ሁኔታ ተችተዋል።

ባራክ በግል ባደረጉት የስልክ ስብሰባ ላይ አሜሪካ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የምታደርገው ጥረት " ቅጥ አምባሩ የጠፋው" ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የቀድሞ ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቻቸው ለጆ ባይደን ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እንዲሰሩ ባበረታቱበት ወቅት እንደሆነ ሲኤንኤን ዘግቧል።

"ለወረርሽኙ ጥሩ የሚባሉ መንግሥታትንም ሊፈትን ይችላል። ነገር ግን ይሄ ወረርሽኝ ለኔ ምንድነው የሚል የግለኝነት ስሜት በዳበረበት ሁኔታና የሁሉንም ፍላጎት አሽቀንጥሮ የጣለ አሰራር በመንግሥታችን ላይ መታየቱ ከፍተኛ ቀውስ ነው" ብለዋል።

ዋይት ሃውስ በምላሹ ፕሬዚደንት ትራምፕ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የወሰዱት እርምጃ የአሜሪካዊያንን ሕይወት ታድጓል ብሏል።

ኦባማ በስልክ ውይይታቸው ወቅት፤ የሪፐብሊካኑ ተተኪያቸው ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የወሰዱት ምላሽ ላይ መንግሥታቸው ተጠያቂ እንደሚሆን አሳስበዋል።

ኦባማ አክለውም በቀድሞ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ማይክል ፍልይን የወንጀል ክስ ለማንሳት የተደረገውን ውሳኔም በጥብቅ ተችተዋል።

ኮሮናቫይረስ በአሜሪካ

እስካሁን ባለው መረጃ በአሜሪካ ከ77 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው ሲያልፍ 1.2 ሚሊየን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። ይህም ከዓለም አገራት ከፍተኛው ነው።

አብዛኞቹ የአገሪቷ ግዛቶች ባለፈው ወር የእንቅስቃሴ ገደብ የጣሉ ሲሆን አሁን ላይ ግን የተጣሉ ገደቦችን እያላሉ እና ሰዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ እየፈቀዱ ነው።

ይሁን እንጅ የጤና ባለሥልጣናት ውሳኔው የቫይረሱን ሥርጭት ሊያባብሰው ይችላል በማለት እያስጠነቀቁ ነው።

የትራምፕ አስተዳደር ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚከተለው ዘዴ ወጥነት የጎደለው ነው። በፈረንጆቹ የካቲት ወር 'ይጠፋል' በሚል የወረርሽኙን አስከፊነት ያጣጣሉት ሲሆን ባለፈው ወር አጋማሽ ላይ ደግሞ ወረርሽኙ አስከፊ መሆኑን ተናግረዋል።

ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ሚያዚያ ፀረ ተህዋስያን ኬሚካል መውሰድ በሽታውን ሊከላከል ይችላል ሲሉ አስተያየት የሰጡ ሲሆን፤ ባለሙያዎች ሃሳባቸውን ውድቅ አድርገውታል።

ባለፈው ሳምንት ደግሞ መንግሥታቸው ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ያቋቋመውን ግብረ ኃይል እንደሚበትኑ አስታውቀው ነበር።

በኋላ ላይ ደግሞ ሃሳባቸውን ለውጠው ግብረ ኃይሉ ሥራውን እንደሚቀጥል በመግለፅ፤ አኮኖሚውን መክፈት ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።