"በፋና ከትግራይ የሚወጡ መረጃዎች ተለቅመው እንዲለዩ ይደረጋል" የመቀለ ፋና ኤፍ ኤም ሥራ አስኪያጅ

የመቐለ ፋና ሥራ አስኪያጅ መሠረት ታደሰ እና የፋና አርማ

የፎቶው ባለመብት, MESERET/FBC

መቀለ በሚገኘው የፋና ኤፍ ኤም ቅርንጫፍ ሬዲዮ ጣቢያ የሚሰሩ ጋዜጠኞችና አመራር አዲስ አበባ የሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት በሥራችን ላይ ጫና እየደረሰብን ነው አሉ።

የመቀለ ፋና ኤፍኤም 94.8 ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ መሰረት ታደሰ "ፋና ሁለት ዓይነት ፋና ሆኗል" ሲል በመቀለው ቅርንጫፍና በአዲስ አበባው ዋና መሥሪያ ቤት መካከል ስለተፈጠረው መለያየት ያስረዳል።

"በመቀለና አዲስ አበባ ያሉ አጀንዳዎች ተለያይተዋል። በሁለቱም የሚሰራጩ ዜናዎችና ዝግጅቶችም የማይገናኙ ሆነዋል" የሚለው ሥራ አስከያጁ፤ በክልሉ ስላሉ ጉዳዮች ሳይሆን ከመሃል አገር ለሚመጡ አጀንዳዎች የቅድሚያ ትኩረትን መስጠት አለባችሁ በሚል ጫና እንደተደረገባቸው መሆኑን ይገልጻል።

ይህንን በመቃወም በተደጋጋሚ ለማስረዳት ቢሞክሩም ከዋናው መሥሪያ ቤቱ በኩል ሰሚ እንዳጡና የድርጅቱን ኤዲቶሪያል ፖሊሲ በማይጥስ መልኩ ለክልላዊና አገራዊ ጉዳዮች ሽፋን መስጠት እንደቀጠሉ ሥራ አስኪያጁ ተናግሯል።

"ድርጅቱ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ፤ እንዲሁም ሌሎች ማንዋሎችና የኢትዮጵያ ብሮድካስት አዋጅ እንደሚለው ከሆነ ሚድያው 60 ከመቶ ለአገራዊ ጉዳዮች ወይም መረጃዎች ሽፋን መስጠት አለበት። ፋና ግን ላለፉት ሁለት ዓመታት አገራዊ አጀንዳዎችን ወደጎን ትቷል" ሲል ይገልጻል- ጋዜጠኛ መሰረት።

ምክንያቱን ሲያስረዳም "ተቋሙ በአዲስ አበባና በከተማዋ ለሚገኘው የፌደራል መንግሥትን የሚመለከቱ አጀንዳዎች ሽፋን በመስጠት ክልላዊ ጉዳዮችን ረስቷል፤ ይህም የመንግሥት ቃል-አቀባይ ሆኖ እንደማገልገል እንቆጥረዋለን" ብሏል።

"በደብዳቤ አሳውቀናል. . . "

ችግሩ ማስተካከያ እንዲደረግበት ከዋናው መሥሪያ ቤት አመራሮች ጋር እንደተነጋገሩና ከአመራሩ የያገኙት መልስ ግን "ከዚህ ለሚሰጣችሁ አጀንዳ ትኩረት ሰጥታችሁ መሥራት አለባችሁ" የሚል እንዶነ አስታውሷል።

የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ መሰረት እንደሚለው፤ በየክልሉ የተከፈቱት የፋና ኤፍኤሞች በየአካባቢያቸው ላሉ ጉዳዮች ሽፋን መስጠት ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ ለሚገኘው ዋናው ማሰራጫም ክልላዊ በዜናም ይሁን በፕሮግራም በመልክ እንዲያቀርቡ በኤዲቶሪያል ፖሊሲውም እንዲሆንም በማንዋሎቹ ሰፍሮ ይገኛል።

"ይሁን እንጂ" ይላል ጋዜጠኛ መሰረት "በመቀለም ይሁን በትግራይ ክልል የሚኖሩ ሁነቶች በዜናና በፕሮግራም መልክ ስንልክላቸው አብዛኞቹ እንዲታገዱ፣ ሌሎቹ በተዛባ መልኩ እንዲቀርቡ፣ አልፎ አልፎም እኛ የዘገብነውን ትተው ሌላ ምንጭ የመጠቀም ሁኔታ አለ" ሲል ስለሁኔታው ይገልፃል።

ይህ ክስተት እየተደጋገመ በመሄዱም በህዳር ወር 2012 ላይ ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት ደብዳቤ በመጻፍ "እኛ የምንልካቸው መረጃዎች ሲታገዱና በተዛባ መልኩ ሲቀርቡ እዚህ ካሉት አድማጮቻችን ጋር ስለሚያራርቁን መሻሻል አለበት። 'ይህ መሆን ካልቻለ ግን ከዚህ ወዲህ የምንልክላችሁ ዘገባ አይኖርም' የሚል መልዕክት አስተላልፈናል" በማለት ይናገራል።

ይሁን እንጂ በህዳር ወር ላይ ለተጻፈ ደብዳቤ እስከ ዛሬ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው የሚናገረው ሥራ አስኪያጁ፤ በእነርሱ በኩልም ወደ ዋናው ማሰራጫ የተላኩ ዘገባዎች እንዳልነበሩ አስታውሷል።

ይህ ዋናው መስሪያ ቤትና በቅርንጫፍ ጣቢያው መካከል ያለው አለመግባባትም ከሁለት ዓመት በፊት እንደጀመረ ሥራ አስኪያጁ ይገልጻል።

"የመንግሥት ለውጥ ከተደረገ ወዲህ ፋና በአካባቢያችን የነበረው ተቀባይነትና ተደማጭነት እየቀነሰ መጥቷል። በዚህ ሁኔታ ውስጥም ሆነን ግን ለአካባቢያችን ይመጥናል የምንላቸውን ይዘቶችና አጀንዳዎችን ማቅረብ ስንጀምር ጉዳዩ እየከረረ ሄደ" መሄዱን ጋዜጠኛ መሰረትአመለክቷል።

ጨምሮም የመቀለው ቅርንጫፍ ከአዲስ አበባ ለሚሰራጩ ፕሮግራሞች በተመደበው የአየር ጊዜ አንዳችም መሸራረፍ ሳያደርግ ሙሉ ሽፋን መስጠቱን አስረድቷል።

እሱ እንደሚለው፤ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ግን በዋናው ማሰራጫ ትግራይን ለሚመለከቱ ዘገባዎች የሚሰጠው ሽፋን ሙሉ በሙሉ እንዲቆም ሆኗል።

የታገዱ ይዘቶች ምን ምን ናቸው?

መቀለ ፋና ኤፍ ኤም ከአዲስ አበባ የሚተላለፉ ፕሮግራሞች በሊንክ እየተቀበለ በመቀለና አካባቢዋ ለሚገኙ አድማጮች የሚያደርስ ሆኖ በቀን ካለው የሥርጭት ሰዓትም ስምንቱን በራሱ ጋዜጠኞች ለሚያዘጋጃቸው ፕሮግራሞች ያውላል። ክልሉን የሚመለከቱ ጉዳዮችም በነዚህ ሰዓታት ሽፋን ያገኛሉ።

አለመግባባቱ የተፈጠረውም በእነዚ ሰዓታት ላይ በሚቀርቡት ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ቁጥጥር መደረግ በመጀመሩ እንደሆነ የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ መሰረት ይናገራል።

"እንዳንሰራቸው ወይም ሽፋን እንዳንሰጣቸው የተከለከልነው ጉዳዮች በርካታ ናቸው። ከትግራይ የሚወጡ መረጃዎች ተለቅመው እንዲለዩ ይደረጋል። አብዛኞቹም እንዳይተላለፉ ይደረጋል" ይላል።

በማስከተልም "ለምሳሌ የክልሉ ምክር ቤት ውሳኔዎች፣ የክልሉ ፓርቲዎች በተለይም የህወሓት መግለጫዎች፣ የክልሉ ሥራ አስፈጻሚዎች የሚሰጧቸው መግለጫዎች፣ የምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ መግለጫዎችና ቃለ-መጠይቆችን በተደጋጋሚ ልከን እንዳይተላለፉ ታግደዋል" ሲል በዝርዘር ያስቀምጣል።

ሌላው ቀርቶ በክልሉ የተካሄዱ ታላላቅ ሕዝባዊ ሰልፎችም በቀጥታና ከተካሄዱ በኋላ የአየር ሽፋን እንዳይሰጣቸው መደረጉንም ገልጿል።

"ሽፋን የተሰጣቸውም ካሉ በተሸራረፈና ባልተባለ መልኩ ሲቀርቡ ታዝበናል። እዚያ ያሉ ጋዜጠኞችም 'የፌደራል መንግሥት በሚመለከት የሚሰጡ አስተያየቶች እንዳትልኩልን' ይሉናል" በማለትም ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, FANA MEKELLE

ማስጠንቀቂያው!

ጋዜጠኛ መሰረት እንደሚለው ጉዳዩ እየጠነከረ በመምጣቱ በሚያዝያ 30/2012 ዓ.ም ከዋና መሥሪያ ቤቱ የተጻፈ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ በግንቦት 1/2012 ደርሷቸዋል። ደብዳቤው ግን በግልጽ ያሰፈረው መልዕክት እንደሌለ ይናገራል።

"ደብዳቤው የሚድያ ተቋሙ 'ኤዲቶሪያል ፖሊሲና መመሪያዎችን አለማክበርና እንዲከበሩ አለማድረግ' ይላል። በዝርዝር ያሰፈረው ነገር የለም፤ ጥቅል ነው። የተጣሰው ነገር ምንድነው? ያልተከበረውስ? የሥራ ዲሲፕሊን ጥሰትም ይላል፤ በማንና መቼ ነው የተጣሰው? የሚሉት በግልጽ አልሰፈሩም" ብሏል።

ደብዳቤው ተፈጽመዋል የተባሉት ጥሰቶች በአስቸኳይ እንዲስተካከሉ ስለሚጠይቅ መታረም ያለባቸው ነገሮች ምን ምን እንደሆኑ በግልጽ ባለመቀመጣቸው "ግልጽ ያልሆነ ደብዳቤ" ሲል ገልጾታል።

የተነሱት ጉዳዮች በግልጽና በዝርዝር እንዲቀመጡም ወደ ዋናው መሥሪያ ቤት ደብዳቤ መላካቸውንም አስታውሷል።

ኤፍቢሲስ ምን ይላል?

ደብዳቤው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ሙለታ ቶላ እንደተጻፈ በስም፣ ፊርማና ማህተም መረዳት ችለናል።

ቢሆንም በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን በስልክ ጥያቄ ያቀረብንላቸው ዋና ሥራ አስኪያጁ "ጉዳዩን በደንብ ስለማላውቀው መልስ መስጠት አልችልም" ብለውናል።

በማስከተልም "ጉዳዩም የውስጥ ጉዳይ ስለሆነ በውስጥ ነው የምንፈታው እንጂ አሁን መናገር አልችልም" በማለት ለተጨማሪ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

የመቀለ ፋና ኤፍ ኤም ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ መሰረት ታደሰ እንደሚለው ከሆነ "የድርጅቱ ስም እየተበላሸ በመምጣቱ ምክንያት ብዙ ጋዜጠኞች ሥራቸውን ለቀዋል። የተቀሩት ደግሞ እነዚህን ፈተናዎች በመቋቋም አሁንም ኤዲቶርያል ፖሊሲውን በመጠበቅና 'ለወራት ስናካሂደው የነበረውን ትግል እናስቀጥላለን' በማለት ሥራቸውን እንደቀጠሉ" ገልጿል።

"አሁን እየመጣ ስላለው ቁጣና ማስጠንቀቂያ ቀድሞውንም እናውቀው ነበር፤ ሙያዊ አቅማችንን በመጠቀምም ትግራይንና የትግራይን ሕዝብ እናገለግላለን። ምናልባት ቅጣት ከመጣም ተዘጋጅተናታል" ብሏል ሥራ አስኪያጁ።

በአገሪቱ ከሚገኙ ጥቂት ግዙፍ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት አንዱ የሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በተለያዩ ስፍራዎች ካሉት የኤፍኤም ጣቢያዎች አንዱ የሆነው መቀለው ቅርንጫፍ ጣቢያ ከተከፈተ 10 ዓመት እንደሆነው ለማወቅ ተችሏል።